የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛሉ

የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግታቸውን ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች ክለቦች ቀድመው ባደረጉት የዝግጅት ጨዋታ ጊዮርጊስ 1ለ0 በማሸነፍ ነበር በቀዳሚነት የዝግጅት ጨዋታዎች መጀመር የቻሉት። በመቀጠል ዓርብ ቢሾፍቱ ላይ ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ ተጫውተው ጅማ አባጅፋር በአዲስ ፈራሚዎቹ መሐመድ-ኑር ናስር እና ኢዮብ ዓለማየሁ ጎሎች 2ለ1 የረቱ ሲሆን ለጦሩ ብቸኛዋን ጎል ጋናዊው አጥቂ ኢማኑኤል ኡኩቱ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ዕሁድ ረፋድ 3፡00 በሀዋሳ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እያደረጉ የሚገኙ አራት ክለቦች የመጀመሪያ የወዳጅነት ጨዋታቸውን አከናውነዋል፡፡ በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ሜዳ ሲዳማ ቡና እና ሰበታ ከተማ ተገናኝተው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ክለብ ሲዳማ 2ለ0 አሸናፊ ሆኗል፡፡ ለሲዳማ ቡና ወጣቱ የመስመር ተጫዋች ተመስገን በጅሮንድ እና ከከፍተኛ ሊጉ ኮልፌ ቀራኒዮ ክለቡን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው ብሩክ ሙሉጌታ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ በተመሳሳይ ረፋድ ላይ በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የዝግጅት ወቅት የመጀመሪያ የሆነውን የወዳጅነት ጨዋታ አድርገዋል፡፡ ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው መርሀግብር 1ለ1 ሲጠናቀቅ ኤፍሬም አሻሞ ለሀዋሳ ከተማ አዲሱ ፈራሚ እንየው ካሣሁን ለድሬዳዋ አስቆጥረዋል፡፡

በቀጣዮቹ ቀናቶችም የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ እና የጎፈሬ ሲዳማ ዋንጫ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጨዋታዎች እንደሚያየርጉ የሚጠበቅ ሲሆን አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ የወዳጅነት ጨዋታ ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር በቀጣዩ ረቡዕ አልያም ሐሙስ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ እቅድ እንደያዙ ሰምተናል፡፡