አዲስ አበባ ከተማ ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማማ

በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ሁለት የውጪ ዜጋን ጨምሮ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምቷል።

ጋብሬል አህመድ ወደ አዲስ አበባ ለማምራቱ ከተስማሙት መካከል ነው፡፡ ጋናዊው የተከላካይ አማካይ በ2003 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በደደቢት የተሳኩ ዓመታት በማሳለፍ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር የተዋወቀ ሲሆን በመቀጠል ወደ ሀዋሳ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ በማቅናት ተጫውቶ ማሳለፍ ችሏል፡፡ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በድጋሚ ለሀዋሳ ከተማ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው ይህ ተጫዋች በ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አዳጊውን ቡድን መቀላቀሉ ተረጋግጧል፡፡

ሌላኛው ጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ ኦዶንጎ መዳረሻው የአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከሩ ክለብ ሆኗል፡፡ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መጫወት ከቻለ በኋላ የኢትዮጵያ ቆይታውን የጀመረው ይህ አጥቂ በመቀጠል በድሬዳዋ ከተማም ተጫውቷል። ተጫዋቹ በምስራቁ ክለቡ ያለውን ቆይታ አገባዶ የመዲናይቱን ክለብ ምርጫው አድርጓል፡፡

ሦስተኛው ከክለቡ ጋር ልምምድ የጀመረው እና ቅድመ ስምምነት የፈፀመው የመስመር አጥቂ እንዳለ ከበደ ነው። ከአርባምንጭ ከተማ የተገኘው እና ባለ ተሰጥኦ ከሚባሉ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀሰው እንዳለ በሲዳማ ቡና ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ከ2012 የውድድር ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ ሲጫወት ካሳለፈ በኋላ ከሁለት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቶ ማረፊያውን አዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ ስምምነትን ፈፅሟል፡፡