ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ | ሰበታ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን አሸንፏል

በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የሁለተኛ ቀን ውሎ ሰበታ ከተማ ሀድያ ሆሳዕናን 2ለ0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

የሁለተኛ ቀን ሁለተኛ የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታ ቀን 9፡00 ሲል በሀድያ ሆሳዕና እና ሰበታ ከተማ መካከል ተደርጓል፡፡ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ የጨዋታ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን በመያዝ ረጅም ደቂቃዎችን ከማሳለፍ በዘለለ ንፁህ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ጥቂቱን ብቻ ነበር፡፡ ጨዋታው በተጀመረ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ የሰበታ ከተማው የመስመር አጥቂ ዱሬሳ ሹቢሳ ቅፅበታዊ የሆነች ሙከራን ሞክሮ መሳይ አያኖ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ ቀዳሚዋ ሙከራ ሆናለች፡፡

ቀስ በቀስ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲመጣ ሀድያ ሆሳዕናዎች መሀል ሜዳ ላይ ሳምሶን ጥላሁን እና አበባየው ዮሀንስ በሚፈጥሩት ጥሩ ቅንጅት ቶሎ ቶሎ ወደ ሰበታ የግብ ክልል ለመጠጋት አልተቸገሩም በተለየ መልኩ ሳምሶን ይከተለው የነበረው የጨዋታ መንገዶች በተደጋጋሚ ለሚፈጥሩት አጋጣሚ ሁነኛው የጥቃት መነሻ ሲሆኑ ተመልክተናል፡፡

ባዬ ገዛኸኝ ባደረጋት የ10ኛ ደቂቃ ሙከራ ወደ ሰበታ የግብ ክልል መጠጋት የጀመሩት ሀድያዎች በሌላ አጋጣሚ ከቅጣት ምት አበባየው መቶ የግቡ የላይኛው ቋሚ ብረት ነክቶ የመለሰበት ሌላኛዋ ተጠቃሿ ነበረች፡፡ 32ኛው ደቂቃ ላይ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ለመከተል በተወሰነ መልኩ ለመሞከር የጣሩት ሰበታ ከተማዎች ጌቱ ኃይለማርያም ከመስመር አሻምቶ ዘካሪያስ ፍቅሬ በግንባር ገጭቶ መሳይ አያኖ የያዘበት በዚህ አጋማሽ የሰበታ ሁለተኛ ሙከራቸው ሆናለች፡፡

ወደ መልበሻ ቤት ሊያመሩ አምስት ደቂቃ ሲቀር ኤፍሬም ዘካሪያስ የሰበታ ተከላካዮችን መዘናጋት ተመልክቶ መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሲመታው ምንተስኖት አሎ የመለሰበት ምናልባት ሀድያ ሆሳዕና መሪ ለመሆን መቃረቡን አመላካች ፍንጭ የምትሰጥ ሆና የነበረች ብትሆንም ያለጎል ተገባዷል፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ምንም እንኳን ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴን መመልከት ብንችልም ሰበታ ከተማ ቤዛ መድህንን በናሚቢያዊው አጥቂ ጂኒያንስ ናንጄቤን ቀይሮ ካስገባ በኋላ የተሻሻለውን ቡድን መመልከት ችለናል በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕናዎች የጨዋታውን ሚዛን መሀል ሜዳ ላይ ባጋደለ መልኩ አዘወትረው ተጠቅመዋል፡፡ 47ኛው ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ሹቢሳ ሞክሮ መሳይ አያኖ ባዳነበት አጋጣሚ ወደ ጎል የደረሱት ሰበታዎች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው ጂኒያንስ ናንጄቤ ከፍፁም ተፈሪ የተቀበለውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ ሰበታን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

የሀድያ ተከላካዮች መዘናጋትን በመጠቀም በድጋሚ ሰበታዎች በፍፁም ተፈሪ አማካኝነት ዕድል ቢያገኙም በሀድያ ሆሳዕና በኩል ድንቅ የነበረው ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል፡፡

 

የተጫዋች ቅያሪ የሰመረላቸው ሰበታ ከተማዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ ጂኒያስ ናንጄቤ ከመሀል ሜዳ የሀድያ ተከላካዮች መዘናጋት ተጠቅሞ ወደ ግብ ክልል እየነዳ ገብቶ ከመሳይ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መሳይ አድኖበታል፡፡ 80ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ መሐል ሜዳ ላይ በሰበታ ከተማው ተከላካይ በረከት ሳሙኤል በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡

ጂኒያንስ ናንጄቤ ተቀይሮ ከገባ በኋላ የሰበታን የማጥቃት ሀይል የጨመረ ሲሆን ናሚቢያዊው አጥቂም በጭማሪው ደቂቃ ላይ በድጋሚ የተከላካዮችን ስህተት ተመልክቶ ብስለቱን በመጠቀም ነፃ አቋቋም ለነበረው ፍፁም ገብረማርያም አቀብሎት አጥቂውም ኳሷን ወደ ጎልነት ለውጧት የሰበታን የጎል መጠን ወደ ሁለት በማሳደግ ጨዋታው 2ለ0 ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀድያ ሆሳዕናው አማካይ ሳምሶን ጥላሁን የጨዋታው ምርጥ በመባል ተሸልሟል፡፡

ያጋሩ