አዳማ ከተማ ግዙፍን ተከላካይ አስፈርሟል

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት አዳማ ከተማዎች ከቀናት በፊት ከወልቂጤ ከተማ ጋር የተለያየውን ተከላካይ በይፋ ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ግቦችን (42) ካስተናገዱ ክለቦች መላከል ግንባር ቀደሙ የሆነው አዳማ ከተማ ይህንን ወሳኝ መስመሩን ለማደስ በዝውውር መስኮቱ ላይ በንቃት ሲሳተፍ ቆይቷል። በዚህም ምንተስኖት አዳነ እና አዲስ ተስፋዬን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ከሰበታ ከተማ ቀድሞ ያስፈረመው ክለቡ ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ በቦታው የሚጫወተውን ቶማስ ስምረቱን በአንድ ዓመት ውል አስፈርሟል።

የቀድሞ የሱሉልታ፣ ወላይታ ዲቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የነበረው ቶማስ 2012 ላይ ወደ ወልቂጤ ከተማ አምርቶ እንደነበር ይታወሳል። ተጫዋቹም ዓምና ሁለት ዓመታትን ከክለቡ ጋር ለመቆየት ፊርማውን አኑሮ የነበረ ቢሆንም በስምምነት ባሳለፍነው ሳምንት ከተለያየ በኋላ በዛሬው ዕለት ማረፊያው አዳማ መሆኑ ታውቋል። እርግጥ ተጫዋቹ ከአዳማዎች ጋር ልምምድ መስራት ከጀመረ ቢሰነባብትም ከደቂቃዎች በፊት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝቶ ስምምነቱን ህጋዊ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ያጋሩ