የቅዳሜው የዋልያዎቹ ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ያገኛል?

የፊታችን ቅዳሜ በባህር ዳር ዓለም አለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገው የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ያገኝ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅረናል።

ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ በምድብ ሰባት የተደለደሉት ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን እርስ በእርስ መስከረም 29 እና ጥቅምት 2 እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በተለይ ቅዳሜ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ያለ ደጋፊዎች እንደሚደረግ መገለፁን ተከትሎ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ጨዋታው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚተላለፍ እና እንደማይተላለፍ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ይህንን የብዙሃን ጥያቄ ተንተርሳ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ጨዋታው የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ ተረድታለች። ቅዳሜ 10 ሰዓት የሚደረገውን ጨዋታም የውድድሩ የበላይ አካል የሆነው ፊፋ በበይነ-መረብ አማካኝነት በፊፋ ቲቪ (ዩ ቱብ ቻነል) አማራጭ በስታዲየም ለማይገኙ የሀገር ውስጥ እና ውጪ የስፖርት ቤተሰቦች ተደራሽ እንደሚያደርግ አረጋግጠናል። ጨዋታውን ለማስተላለፍም ከፊታችን ባሉት ቀናት የውጪ ሀገር የቀረፃ እና የስቱዲዮ ባለሙያዎች ወደ ሀገራችን እንደሚገቡም ተጠቁሟል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጳጉሜ 2 በኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ጨዋታ ላይ ያጋጠመው ድንገተኛ የሳተላይት ችግር በአሁኑ ጨዋታም እንዳይከሰት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ታውቋል።

ከፊፋ ቲቪ ውጪ ጨዋታው በሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመተላለፉ ዕድል ግን ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ጠባብ እንደሆነ እና ማረጋገጫ እንዳላገኘ ሰምተናል።

ያጋሩ