ሳዲቅ ሴቾ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ይናገራል

ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ በተመረጠ ከተማ በሚደረግ በማጠቃለያ ውድድር ድሬዳዋ ከተማ ላይ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ ከሚመራው ሼር ኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ ቡና 2008 ላይ ተቀላቀለ። ኢትዮጵያ ቡና በቆየባቸው ዓመታት በርከት ባሉ ጨዋታዎች አይሰለፍ እንጂ በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በተለይ ደደቢት ላይ የሰራው ሐት-ትሪክ አሁንም ድረስ በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ ይታወስለታል። በማስከተል ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት ከጉዳት ጋር የታጀበ ያልተሳካ ቆይታ በማድረግ ዓምና ግማሽ ዓመት ላይ በከፍተኛ ሊግ ለአዲስ አበባ ከተማ መጫወት ችሏል። ዘንድሮ አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማን በመቀላቀል ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የመጫወት ዕድሎችን በማግኘት ቡድኑ ከወራጅ ቀጠና የሚወጣበት ወሳኝ ጎሎችን እያስቆጠረ ይገኛል። ሳዲቅ ሴቾ አሁን ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ እና ስለቀጣይ እቅዱ ይናገራል።

በቅድሚያ ኢትዮዽያ ቡና ስለነበረህ ጊዜ ትንሽ አጫውተኝ

በኢትዮጵያ ቡና በነበረኝ ቆይታ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ከታችኛው ሊግ ወደ በርካታ ደጋፊ ወዳለው ቡድን ስትመጣ የሚኖረው ጫና ከባድ ቢሆንም በማገኛው የመጫወት ዕድሎች ሁሉ ጎል በማስቆጠር አቅሜን ለማሳየት ሞክሬያለው። ሆኖም በወቅቱ የውጭ አጥቂዎች በብዛት ቡድኑ ውስጥ በመኖራቸው ምክንያት በቂ የመሰለፍ ዕድል ማግኘት አልቻልኩም። ያም ቢሆን ቡና በነበረኝ ቆይታ ደስተኛ ነበርኩኝ።

ከቡና ጋር ከተለያየህ በኃላ ያልተሳካ ጊዜ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አሳልፈህ ለከፍተኛ ሊጉ አዲስ አበባ ከተማ መጫወት ችለሀል…

አዎ በእርግጥ ከኢትዮዽያ ቡና ወጥቼ ወደ ሀዋሳ ከተማ ነው ያመራሁት። ከሀዋሳ ጋር አጀማመሬ ጥሩ ነበር። በደረሰብኝ ጉዳት ለተወሰነ ጊዜ ለማገገም ከብዶኝ ነበር። በዚህም በሚፈለገው መልኩ ለሀዋሳ በቂ አገልግሎት መስጠት ባለመቻሌ በስምምነት ስድስተኛ ወር ላይ ለመለያየት ችያለው። በመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ከተማ ነው ያመራሁት። አዲስ አበባ በጣም ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት እንደ ቡድን ውጤቱ ጥሩ ባይሆንም በግሌ ጎሎችን እያስቆጠርኩ የተሻለ ቆይታ አድርጌያለው። ያም ይመስለኛል ወደ ወልቂጤ እንድመጣ ያስቻለኝ።

ወልቂጤ ከመጣህ በኃላ የመሰለፍ እድል አላገኘህም ነበር። ምንድነው ምክንያቱ?

አዎ ይሄ የሆነው ከእኔ የተሻለ ተጫዋች በመኖሩ ምክንያት ነው። አጥቂው ጃኮ አራፋት ከእኔ በተሻለ ጥሩ ጌዜ ላይ ይገኝ ነበር። ኳስ ነው አንዳንዴ ጥሩ ትሆናለህ አንዳንዴ ላይመጣልህ ይችላል። እኔ ደግሞ ከቡድኑ ጋር ዘግይቼ ዝግጅት በመግባቴ ቅድሚያውን ወስዶ የነበረው ጃኮ በመሆኑ ያልተጫወትኩባቸው ጨዋታዎች ነበሩ።

አሁን የመሰለፍ እድሎችን እያገኘህ መጥተሀል። ቡድንህ ከወራጅ ቀጠና እንዲወጣ በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ወሳኝ ጎሎችን እያስቆጠርክ ትገኛለህ። አሁን ስላለህበት ወቅታዊ አቋም ግለፅልኝ?

ከድሬዳዋ ጨዋታ ጀምሮ ነው የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኜ መግባት የጀመርኩት። ከዛ በፊት ጃኮ ቋሚ ስለነበር ተቀይሬ ነበር እጫወት የነበረው። እንደምታቀው ቡድኑ ውጤት እየራቀው በጣም አጣብቂኝ ውስጥ በገባንበት በዚህ ሰዓት ነው በድሬደዋ ጨዋታ ላይ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ ገብቼ ወሳኙን የማሸነፊያ ጎል ማስቆጠር የቻልኩት። ከሆሳዕና ጋር በነበረው ከባድ ጨዋታም ጎል ማስቆጠር ችያለው። አሁን የመጫወት እድሉን አሰልጣኜ ሰጥቶኛል፤ ከዚህ በኃላ እድሉን በአግባቡ መጠቀም የእኔ ፈንታ ነው። በቀጣይም ከፈጣሪ ጋር ከዚህ በተሻለ ቡድኔን ለማገልገል የምችለውን ሁሉ አደርጋለው።

ወልቂጤ ለሊጉ አዲስ ነው። አጀማመሩ ጥሩ ባይባልም ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና በመውጣት እየተነቃቃ ይገኛል። በቀጣይ ወልቂጤ በሊጉ እንዲቆይ በግልህ እና ከቡድን አጋሮችህ ጋር ምን ታስባለህ?

ቡድናችን ውስጥ የሚገርም ኅብረት እና አንድነት አለ። ሁሉም ተጫዋች ከቡድኑ ጋር ረዥም ዓመት አብረው የቆየ ነው የሚመስለው። አስተዳደሩም እግርኳስን በሚገባ በሚያቁ ሰዎች የተሞላ ነው። ቡድኑ በአጠቃላይ ስመለከተው ለሊጉ አዲስ አይመስልም። እኛ ስለ መውረድ አናስብም ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ነው ዕቅዳችን። በግሌም እንደ ቡድንም የምንችለውን በማድረግ ቡድናቸውን በመደገፍ ከማይደክማቸው ደጋፊዎቻችን ጋር በመሆን በቀጣይ ጨዋታዎች ደረጃችንን የበለጠ እናሻሽላለን ብዬ አስባለው።


©ሶከር ኢትዮጵያ