ስንታየሁ መንግስቱ ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ይርቃል

የወላይታ ድቻው ወሳኝ አጥቂ በጉዳት ምክንያት ረዘም ያለ ጊዜ ከሜዳ እንደሚርቅ ተጠቁሟል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር አስገራሚ ግስጋሴ እያደረጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን እግር በእግር እየተከተለ ራሱን በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ማግኘቱ ይታወቃል። በነገው ዕለት ደግሞ በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ብቻ ከሚያንሰው ሀዋሳ ከተማ ጋር ወሳኝ ጨዋታውን ያደርጋል። ከዚህ ወሳኝ ጨዋታ በፊት በተሰማ ዜና ደግሞ ቡድኑ ወሳኙን ተጫዋች ስንታየሁ መንግስቱን ከወር በላይ እንደሚያጣ ይጠቁማል።

1206 ደቂቃዎችን የጦና ንቦቹን ዘንድሮ ያገለገለው ስንታየሁ ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገው የድሬዳዋ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ በ63ኛው ደቂቃ በአበባየሁ አጪሶ ተቀይሮ መውጣቱ አይዘነጋም። ተጫዋቹ ያጋጠመው የጉልበት ጉዳት በራጅ ከታየ በኋላም ጠንከር ያለ መሆኑ በመታወቁ ለአንድ ወር እረፍት እንዲያደርግ በህክምና ባለሙያዎች እንደተነገሩት አውቀናል። ምናልባት የራጁ ውጤት በቂ ካልሆነ በቀጣዩ ሳምንት የኤም አር አይ ምርመራም እንደሚያደርግ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አምስት ጎል እና ሁለት አሲስት በስሙ ያስመዘገበው ተጫዋቹ አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ በአዳማ ከተማ ቡድኑ ከሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰበታ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የማይኖር ይሆናል።