አህመድ ሁሴን ከሜዳ የሚርቅበት ጊዜ ታውቋል

አርባምንጭ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር 4 አቻ ሲለያይ ለአዞዎቹ ሦስት ጎል አስቆጥሮ ድንቅ ጊዜን በማሳለፍ በጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ የወጣው አጥቂው አህመድ ሁሴን አሁን ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ አጣርተናል።

ከአሰላ ከተማ የተገኘው አህመድ ሁሴን 2011 ላይ በከፍተኛ ሊግ በወቅቱ ተሳታፊ ወደ ነበረው ወልቂጤ ከተማ አምርቶ ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያድግ ግቦችን በማስቆጠር ትልቅ ድርሻ ነበረው። ቁመተ ረጅሙ አጥቂ ከ2012 እስከ ዘንድሮ የ2014 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛውን ዙር ጨዋታዎችን በወልቂጤ ከተማ መለያ በማሳለፍ ቀሪ የስድስት ወራት ውል እየቀረው ሦስት አመት ከመንፈቅ የቆየበትን ክለብ ከወር በፊት በመልቀቅ ወደ አርባምንጭ ከተማ አምርቶ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

በትላንትናው ዕለት አርባምንጭ ከተማ በ18ተኛው ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ጨዋታውን አድርጎ እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ 4ለ1 ሲመራ ተጫዋቹ እስከ 72ተኛው ደቂቃ ድረስ ለክለቡ በቋሚነት ተሰልፎ ሦስት ጎሎችን አስቆጥሮ ሀትሪክ መስራት ቢችልም ጨዋታው በጉዳት እሱን ካጣ በኋላ በአስገራሚ ሁኔታ 4ለ4 ተጠናቋል፡፡ ከሀድያ ሆሳዕናው ተከላካይ ፍሬዘር ካሣ ጋር 72ተኛ ደቂቃ ላይ ኳስን በአየር ላይ ለማግኘት በሚዘልበት ጊዜ ጉዳት ገጥሞት በአምቡላንስ ወደ ህክምና ጣቢያ ያመራውን አጥቂ ዛሬ ረፋድ አግኝተን በምን አይነት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠይቀነው በአጭሩ ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡

“ዘልዬ ስመለስ ኳሷን ለማግኘት ጥረት ሳደርግ በጎን አረፍኩኝ። በዚህም ጉዳት ገጠመኝ። ማታ ትንሽ እያመመኝ ነበር፡፡ ራጅ ተነስቼ ቁርጭምጭሚቴ ላይ ጅማት ተበጥሷል ነው የተባልኩት፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም አንድ ወር ከአስራ አምስት ወይም እስከ ሁለት ወር በሚደርስ ጊዜ ከሜዳ ያርቅሀል ብለውኛል፡፡ አዳማ ጀነራል ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና አሁን ልሄድ ነው። ከማታው አንፃር አሁን ትንሽ ይሻለኛል። ማታ ግን ሳልተኛ ነበር ያደርኩት። አሁን ግን ህመሙ ምንም አይልም።” ሲል ያለበትን ሁኔታ ነግሮናል፡፡