ወልቂጤ ከተማ ሁለት ተከላካዮችን አስፈረመ

የመቐለ 70 እንደርታ ሁለት ተከላካዮች በአንድ ዓመት ውል ሠራተኞቹን ተቀላቅለዋል፡፡

አዲስ አበባ ከትመው ለ2013 ቢትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዝግጅታቸውን መሥራት ከጀመሩ ወራት ያስቆጠሩት ወልቂጤ ከተማዎች ሁለት ተከላካዮችን በይፋ አስፈርመዋል፡፡ አንጋፋው ተከላካይ ሥዩም ተስፋዬ አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ሆኗል፡፡ የቀድሞው የኤሌክትሪክ፣ ደደቢት እና ከ2010 ጀምሮ ለመቐለ 70 እንደርታ እየተጫወተ የቆየው እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም አይረሴ ጊዜን ያሳለፈው ተከላካዩ የመቐለ 70 እንደርታን በሊጉ ያለመሳተፍ ተከትሎ ወደ ወልቂጤ አምርቷል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ አሚኑ ነስሩ ነው፡፡ የቀድሞው የሀዲያ ሆሳዕና፣ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ ተከላካይ ከሰሞኑ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ልምምድ ሲሰራ ከቆየ በኃላ በዛሬው ዕለት በይፋ የክለቡ ተጫዋች መሆኑን ፌድሬሽን በመገኘት አፅድቋል፡፡

ክለቡ ሌላኛው ተከላካይ አሌክስ ተሰማን ለማስፈረም አቅዶ ተጫዋቹም ልምምድ ሲሰራ ከሰነበተ በኃላ ምርጫውን ወደ ሌላ ክለብ በማድረጉ ሳይፈርም መቅረቱን የክለቡ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ