የጨዋታ ሪፓርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፏል 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ በእኩል 16 ነጥብ 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪክን እና ድሬዳዋ ከተማን 09:00 ላይ አገናኝቶ ኤሌክትሪክ 3-1 በሆነ ውጤት ተጋጣሚውን መርታት ችሏል፡፡ በጨዋታው ከተቆጠሩ 4 ጎሎች መካከል ሶስቱን ያስቆጠሩት “በረከት” የሚል መጠርያ ያላቸው ተጫዋቾች መሆናቸው የጨዋታው አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡

በዛሬው ጨዋታ ኤሌክትሪክ በተለመደ አቀራረብ ወደ ሜዳ ሲገባ ድሬዳዋ ከተማዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት ዝርግ 4-4-2 የተጫዋቾች አደራደር ወደ 4-2-1-3 አሰላለፍ ቀይረው በመግባት ከወትሮው በተለየ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ከኤሌክትሪክ በተሻለ ቶሎ ቶሎ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል መድረስ ቢችሉም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ ኤሌክትሪኮች በተለይም በአማካያቸው ዳዊት እስጢፋኖስ በረጃጅሙ ለአጥቂዎቻቸው ኳስ ለማድረስ ጥረት ቢያደርጉም አጥቂዎቹ በተደጋጋሚ በድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች የጨዋታ ውጪ ወጥመድ ውስጥ ሲወድቁ ተስተውሏል፡፡

በ30ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው የመስመር አጥቂው ሱራፌል ዳንኤል የግሉን ጥረት ተጠቅሞ ወደ ኤሌክትሪኮች የግብ ክልል ደርሶ በተቃራኒ አቅጣጫ ለነበረው በረከት ያቀበለውን ኳስ በረከት ይስሃቅ ተረጋጋቶ በቀድሞ ክለቡ ላይ አስቀጥሮ ድሬዳዋን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በቀሩት ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ችለው ነበር፡፡ ሆኖም በ43ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ የድሬዳዋው ተከላካይ ዘላለም ኢሳያስ በግንባሩ ገጭቶ ሲመለስ ከድሬዎች ግብ ክልል ውጪ በቅርብ ርቀት ብቻውን የነበረው በረከት ተሰማ በቀጥታ ኳሷ አየር ላይ እንዳለች መሬት ሳትነካ አክርሮ በመምታት ማራኪ ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተመሪነት ወደ መሪነት ለመሸጋገር የሁለተኛው አጋማሽ መጀመር ብቻ አስፈልጎታል፡፡ በ46ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የድሬዳዋው ተከላካይ በረከት ሳሙኤል ለማውጣት ሲሞክር ሸርፎ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ኤሌክትሪክ 2-1 መሪ መሆን ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር 2 ደቂቃ በኃላ በረከት ሳሙኤል በተመሳሳይ በሰራው ስህተት የተገኘችውን ኳስ ኢብራሂም ፎፉኖ አግኝቶ የሞከራትን ኳስ ሳሞሶን አሰፋ አድኖበታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ በተቆጠረባቸው ግብ የተነሳ ድሬዳዋ ከተማዎች ተነሳሽነታቸው ወርዶ ደካማ የሚባልን እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡ በአንጻሩ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው የበለጠ ጫናን ፈጥረው ተጫውተዋል፡፡ በዚህም በ74ኛው ደቂቃ ፍፁም ገብረማርያም ከሙሉአለም ጥላሁን የተሻገረለትን ኳስ ከግቡ አናት በላይ የሰደደታት እንዲሁም በ76ኛው ደቂቃ በኃይሉ ተሻገር ከግብ ክልል ውጪ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሳሞሶን ያዳናት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል በ78ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በረከት ይስሃቅ በሚያስገርም ሁኔታ ነፃ ሆኖ ቢያገኘውም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ኤሌክትሪክን በውድድሩ አጋማሽ ከዳሽን ቢራ የተቀላቀለው ተክሉ ተስፋዬ በጥሩ ሆኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም በቀላሉ ደገፍ በማድረግ የኤሌክትሪክን አሸናፊነት ያረጋገጠችዋን ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በዚህ ድል መሠረት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ19 ነጥብ ደረጃውን ወደ 7ኛ ከፍ ማድረግ ሲችል ድሬዳዋ ወደ ወራጅ ቀጠናው ለመግባት ተገዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *