በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀዋሳ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ በሀዋሳ ፍፁም የበላይነት 4-0 ተጠናቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ንግድ ባንክን የተቀላቀለው የቀድሞው ሀዋሳ ከተማ አምበል ግርማ በቀለ ጨዋታ ባያደርግም ከሀዋሳ ደጋፊዎች ጋር የሚሰነባበትበትን እድል እግኝቷል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ሀዋሳ ከተማ ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ከባንክ ተሽሎ ታይቷል፡፡ ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩም የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ውጤት መለወጥ ላይ ተሳክቶላቸው ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ፈጥረዋል፡፡ በተለይ ደስታ ዮሀንስ ከመስመር ያቀበለውን ኳስ ጃኮ አራፋት ያባከነው ኳስ የመጀመርያ ጎል ልትሆን የተቃረበች ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ገና በ12ኛው ደቂቃ አዲሱ ሰይፉን መጎዳት ተከትሎ ዳንኤል አድሀኖምን ቀይረው ለማስገባት ተገደዋል፡፡
በ14ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን በተከላካዮች መሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ መድሀኔ ታደሰ ወደ ግብነት ለውጦ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከጎሉ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች ለተጨማሪ ግብ በጋዲሳ መብራቴ እና ፍሬው ሰለሞን አማካኝነት የማጥቃት ጫና መፍጠር ችለው ነበር፡፡ የሀዋሳ ጫናም ፍሬ አፍርቶ ከ4 ደቂቃዎች በኋላ መሪነታቸውን ማስፋት ችለዋል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት ከታፈሰ ሰለሞን ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ውስጥ በመግባት ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል፡፡
በ33ኛው ደቂቃ በሀዋሳ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ታፈሰ ሰለሞን ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ የሰጠውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን በአግባቡ ተቆጣጥሮ በኢማኑኤል ፌቮ መረብ ላይ አሳርፎ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድጓል፡፡
በግብ እና ድንቅ እንቅስቃሴ የታጀበው የመጀመርያ አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ከ3-0 በላይ በሆነ መሪነት እረፍት የሚወጣባቸውን አጋጣሚዎች ፈጥሯል፡፡ በተለይም በ44ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን የሞከረውና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ሙከራ ተጠቃሽ ነበር፡፡ በጨዋታው ተዳክመው የቀረቡት ንግድ ባንኮች በበኩላቸው በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃ ታድዮስ ወልዴ ከሞከረው ውጪ ተጨማሪ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ የመጀመርያው አጋማሽ በሀዋሳ 3-0 መሪነት ተገባዷል፡፡
የሀዋሳ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ቀጥሎ በ52ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በግል ጥረቱ እየገፋ ገብቶ የመታው ኳስ ወደግብነት ቀይሮ የግብ ልዩነቱን ወደ አራት አሳድጎል፡፡ ከግቧ በኃላም በታፈሰ ሰለሞን እና ዳንኤል ደርቤ አማካይነት ግብ የሚሆኑ እድሎችን ሲያመክኑ ተስተውሏል፡፡ መድሃኔ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው ፍርድአወቅ ሲሳይ ከግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረው ኳስ የሀዋካን መሪነት ይበልጥ ሊያሰፉ የሚችሉ ነበሩ፡፡
ንግድ ባንኮች በአንፃሩ በሻኪሩ አማካይነት ከሞከሩት ቀላል የግብ ሙከራ ውጪ በአንደኛው አጋማሽ የነበረው ደካማ እንቅስቃሴ በዚህኛውም አጋማሽ ደግመውታል፡፡ ቢንያም በላይ በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ከደጋፊው ዘንድ አድናቆትን ከማስገኘቱ ውጪ የቡድኑ ተጫዋቾች የተናጠል እንቅስቃሴም ደካማ ነበር፡፡
በደካማ አቋም የውድድር ዘመኑን ለጀመረው ሀዋሳ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ጣፋጭ 3 ነጥብ ከማሳካቱ በተጨማሪ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በከፍተኛ የግብ ልዩነት በማሸነፍ ቀዳሚው መሆን ችሏል፡፡