በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት በተቀራራቢ የነጥብ ልዩነት ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጥረት የተሞላበት እና ጉሽሚያ የበዛበት ይህ ጨዋታ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያሳየን ሲሆን የተሳካ ቅብብል እንኳን በቅጡ ያልተመለከትንበት ጨዋታ ሆኖ ተጠናቋል፡፡
እንግዶቹ አዳማ ከተማዎች በ 4-3-3 የተጫዋቾች አደራደር ወደ ሜዳ ሲገቡ ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች በ3-5-2 አሰላለፍ ለጨዋታው ቀርበዋል፡፡ በጨዋታው የመጀመርያ 15ኛ ደቂቃ ብዙም ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በ5ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ቃልቦሬ ባጋጠመው ከፍተኛ ጉዳት ለተጨማሪ ህክምና በአንቡላስ ወደ ሆስፒታል አምርቷል።
ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረው ጨዋታ እየተጋጋለ ቀጥሎ እንግዶቹ አዳማዎች በጠንካራ መከላከል ውስጥ የሚፈጥሩት የማጥቃት አጋጣሚ በዳዋ ሁቴሳ አማካኝነት እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸው በቀኝ መስመር በግሩም እንቅስቃሴ ሰብሮ በመግባት የሚፈጥረው የጎል አጋጣሚ በጎል አይታጀብ እንጂ መልካም ነበር። ሲዳማዎች በበኩላቸው በጎል ክልላቸው ውስጥ ከሚያደርጉት የኳስ ማንሸራሸር በቀር ወደ ፊት የሚጣሉ ኳሶች መድረሻቸው አይታወቅም ነበር። ያም ቢሆን ትርታዬ ደመቀ 23ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ ገጭቶ ጃኮ ፔንዜ ያዳነበት ፤ በ43ኛው ደቂቃ ላይ በግምት 25 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ሳውሬል ኦልሪሽ መትቶ በድጋሚ እንደምንም ጃኮ ፔንዜ ያዳነው የሲዳማ ቡና መልካም የጎል አጋጣሚዎች ነበሩ።
የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ሊጠናቀቀቅ ተጨማሪ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተመታው ኳስ ሲመለስ ወሰኑ ማዜ በግራ እግሩ መሬት ለመሬት በመምታት ጎል አስቆጥሯል። ጎሉ ለግራ መስመር ተከላካዩ ወሰኑ በሁለት ተከታታይ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የጎሉን መቆጠር ተከትሎ የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ ነው ጎሉ የተቆጠረው በማለት የዕለቱን ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ላይ ቃውሞቸውን አሰምተው የመጀመርያው አጋማሽ በሲዳማ ቡና 1-0 በሆነ ውጤት እረፍት ወጥተዋል።
ከእረፍት መልስ አብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በውዝግብ ፣ በሽኩቻ የተሞላ ነበር፡፡ ይህን ለማብረድ እና ለማረጋጋት የወሰደው ጊዜም የጨዋታው አሰልቺ ጎን ነበር።
በዚህ አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ተዳክመው የቀረቡ ሲሆን ምናልባትም ውጤቱን ከመፈለግ የተነሳ ሙሉ ለሙሉ መከላከልን መምረጣቸው አዳማዎች በተሻለ መልኩ ተጭነው እንዲጫወቱ ረድቷቸዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ዳዋ ሁቴሳ እና አዲስ ህንፃ የፈጠሩት ግልፅ የጎል እድሎች ወደ ግብነት ቢለወጡ የጨዋታው መልክ የተለየ ይሆን ነበር፡፡ ሲዳማ ቡናዎች በአንፃሩ በመልሶ ማጠቃት በአዲስ ግደይ አማካኝነት ጎል ሊሆን የሚችሉ ሦስት ሙከራዎችን አምክኗል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ድሉ ሲዳማ ቡና በ31 ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡን 2ኛ ደረጃ እንዲቆናጠጥ ሲያደርገው ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም መልሶ ወደ 4 ማጥበብ ችሏል፡፡
አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና
“በጨዋታው በተመዘገበው ውጤት በጣም ተደስተናል፡፡ ይህን ውጤታችንንም አጠናክረን እንቀጠላለን፡፡ ከሜዳ ውጭ የነበረብንን ድክመት እያስተካከልን በመምጣትማሸነፍ ጀምረናል፡፡ ቡድኔ ውስጥ ያለው በራስ መተማመን እየጨመረ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው። አሁን በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ገብተናል፡፡ እስከ መጨረሻውም በዚሁ እንቅስቃሴ እንቀጥላለን”
“በዳኝነቱ ላይ ቅሬታ አለን፡፡ ባለቀ ጨዋታ ነው ጎል የተቆጠረብን። በዚህ ጨዋታ ነጥብ እንጥላለን ብለን አላሰብንም ነበር። ሆኖም የጨዋታው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። በቀጣይ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን”