የሀዋሳ ከተማው አማካይ ሙሉጌታ ምህረት ይህ አመት የተጫዋችነት ህይወቱ የመጨረሻው የውድድር ዘመን እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡
ሀዋሳ ከተማ በመጪው አርብ ከዳሽን ቢራ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ሙሉጌታ ምህረት የመጨረሻ ጨዋታውን በደጋፊዎቹ ፊት እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን ክለቡ የመሸኛ ፕሮግራም ለማዘጋጀት እየተዘጋጀ እንሆነም ተሰምቷል፡፡
ሙሉጌታ ምህረት በ1992 የውድድር ዘመን ወደ ሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ለ17 የውድድር ዘመናት በትልቅ ደረጃ መጫወት የቻለ ሲሆን ባለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ምርጥ አማካዮች አንዱ መሆን ችሏል፡፡
ሙሉጌታ የተጫዋችነት ዘመኑን በሀዋሳ ከተማ በሶስት የተለያዩ ጊዜያት (ከ1992-1997 ፣ ከ1999-2001 ፣ ከ2004-2008) ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ (1998) ፣ በደደቢት (2002-2003) እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋችነት አሳልፎ 3 የፕሪሚየር ሊግ ፣ 2 የጥሎ ማለፍ እና የሴካፋ ዋንጫን አንስቷል፡፡ በግሉም በ1996 እና 1999 የፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡
ሙሉጌታ በተጫዋችነት ህይወቱ እና የወደፊት እቅዱ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡
ጫማህን ለመስቀል ያነሳሳህ ምክንያት ምንድነው? ውሳኔ ላይ ለመድረስስ አልተቸገርክም?
አሁን አንተን እስካወራሁህ ጊዜ ድረስ ለውሳኔ ተቸግሬያለሁ፡፡ እግርኳስን መጫወት አቆምኩ ማለት ከኳስ እርቃለው ማለት አይደለም ፤ በእግር ኳሱ ውስጥ የመስራት አላማውና ሀሳቡ አለኝ፡፡ ይህም ቢሆን ተቸግሬያለው፡፡ ቤተሰቤ ፣ ጓደኞቼ እና በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ‘ተጫወት ፣ አቅሙ አለህ’ እያሉኝ ነው፡፡
ለኔ ኳስ መጫወት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ስጫወት እንዴት እግርኳሱ የሚፈልገውን አማሏለው ወይ የሚለውን ማየት እፈልጋለው፡፡ እኔ ብቻ ስለተመቸኝ ወይም ሜዳ ላይ ሰው ስለተመቸው አይደለም፡፡ ክለቡ ከኔ የተሻለ ወጣቶች አያገኝም ወይ የሚለውም መታየት አለበት፡፡ ሌላው አቋሜን አሟጥጬ ማቆም አልፈልግም፡፡ ጥሩ ተጨዋች ሆኜ ማቆም እፈልጋለው፡፡ ነገ ላይ ሙሉጌታ አቋሙ ወረደ መባል አልፈልግም ፤ በጥሩ ሁኔታ ማቆም እፈልጋለው፡፡ ከክለቤ ጋር የአንድ አመት ኮንትራት ስለሚቀረኝ ክለቡ ከፈቀደልኝ በዚህ ሳምንት ጫማ መስቀሌ ይፋ ይሆናል፡፡
ከ15 አመት በላይ የቆየው የተጫዋችነት ህይወትህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ከ15 አመት በላይ በኳስ ተጫዋችነት አሳልፌያለሁ፡፡ ስጀምር ብዙ ውጣ ውረድ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ እግር ኳስን በጀመርኩበት ጊዜ በነበሩ ተጨዋቾች እገዛ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ደርሻለው፡፡ በጥሩ እና በተሳካ ሁኔታ ከ15 አመት በላይ መጫወት ለኔ ኩራት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ቆይታዬ ብዙ ወጣት ተጨዋቾች እንደ ምሳሌ ያነሱኛል ፤ ይህም ለኔ ኩራት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን እግርኳስ ስጀምር መነሻ የሆኑኝ ተጨዋቾች ትልቅ እገዛ አድርገውልኛል፡፡ በአጠቃለይ ጥሩ የእግር ኳስ ህይወት ዘመን ነበረኝ፡፡
ለረጅም ጊዜ በጥሩ ብቃት የመጫወትህ ምስጢሩ ምንድን ነው?
ያው አንድ ተጫዋች አላማ ካለው አላማውን ከግብ ለማድረስ እግርኳሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በከፊልም ቢሆን ለማድረግ ሞክሬያለው፡፡ ሙሉ ለሙሉ አድርጌያለው ባልልም ማድረግ የሚገባኝን ለማድረግ ሁሌም እጥራለው፡፡ ከዚያ በላይ ግን ደግሞ በጣም የምወዳቸው ቤተሰብ አሉኝ ፤ እግር ኳስን በሀዋሳ ስጀምር በጥሩ አጀማመር ነው የጀመርኩት በዚህም ቤተሰቦቼ ደስተኞች ነበሩ ፤ ያን ተከትሎ ሁልጊዜም ቤተሰቦቼን ለማስደሰት በሚል ጠዋትም ማታም መስራት ጀመርኩ፡፡ በየጨዋታው ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ሲደሰቱ ማየት ስለምፈልግና እራሴን ከአልባሌ ነገሮች ቆጥቤ ሁሌም ስራዬን አክብሬ መስራቴ እዚህ ላለሁበት ደረጃ ደርሻለው፡፡ ሚስጥሩ ይህ ነው፡፡
በሀዋሳ ፣ በደደቢት ፣ በብሄራዊ ቡድን (ሴካፋ) እና በቅዱስ ጊዮርጊስ በዋንጫ የታጀቡ መልካም አመታትን አሳልፈሃል፡፡ በግልህ ኮከብ ተጫዋች ሆነህ ያጠናቀቅክባቸው አመታትም አሉ፡፡ በአንተ አእምሮ ተቀርፆ የቀረው ምርጥ አመት የቱ ነው?
በተጫወትኩባቸው ክለቦችም ሆነ ከብሔራዊ ቡድን ጋር ስኬታማ ሆኛለው፡፡ በርግጠኝነት ስኬታማ ከሆኑኩባቸው አመታት እጅግ የማይረሳውና ከአይምሮዬ የማይጠፈው በ1996 ከሀዋሳ ጋር የመጀመርያው የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ባነሳሁበት ጊዜ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ከዛም የሴካፋ ሻምፒዮን ስሆን ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ከዛ በኋላ በጊዮርጊስ እና በደደቢት የማይረሱ ጊዚያትን አሳልፌያለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስትገባ ዋንጫ እንደምታነሳ እርግጠኛ ትሆናለህ ፤ ደደቢትም የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አንስቻለው፡፡ ይህ ሁሉ የመጀመርያውን ዋንጫ ከሳምኩ በኋላ ስለሆነ እንደ መጀመርያው አይሆንልኝም፡፡
በተጫዋችነት ዘመኔ ሳላሳካው አልፌዋለሁ የምትለው ወይም የሚፀፅትህ ነገር አለ?
በእግር ኳስ ታሪኬ ውስጥ አላሳካሁም ብዬ የምፀፀትበት ነገር የለም፡፡ ሌላው ግን በክለብም በብሔራዊ ቡድን ብዙ ጊዜ ተጫውቼ አሳልፌለው ፤ ያኔ በነበረውና አሁን ላይ ባለው የእግር ኳስ ሁኔታ ብዙ ልዩነት አለ፡፡ አሁን እግርኳሱ ተነቃቅቷል ፤ የህዝቡም ፍላጎት ጨምሯል ፤ ብሔራዊ ስታድየሞች ተገንብተዋል ፤ የእግርኳስ እውቀታችን ጨምሯል ፤ እግር ኳሱም ቢሆን ፍጥነቱ ጨምሯል፡፡ በአጠቃላይ አሁን ላይ ያለውን ድባብ ስታይ አሁን ላይ ብጫወት ብለህ ታስባለህ፡፡ ያም ቢሆን ሁሉን አሳክቼ ስለመጣው ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህ ቀረ ብዬ አልፀፀትም፡፡
ካሳለፍከው የእግርኳስ ልምድ አኳያ ወጣት ተጫዋቾች ካንተ ሊማሩ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው?
አዕምሯቸውን ክፍት ማድረግና አሰልጣኝ የሚሰጣቸውን ስልጠና መቀበል አለባቸው፡፡ ይህን ካደረጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይለወጣሉ፡፡ አዕምሯቸውን የሚዘጉ ከሆነ ምንም ነገር መቀበል አይችሉም፡፡ በእግር ኳስ የምትሰራው ለአንድ ወይም ሁለት ሰአት ነው ፤ በዚያች ጊዜ ውስጥ አሰልጣኙና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ስራዎች መስራት አለባቸው፡፡
እኔ ለዚህ የበቃሁት እነ ሰብስቤ ደፋር ፣ ገረሱ እና አፈወርቅ የሚነገሩኝን እየሰማሁ ነው፡፡ ዛሬም ሲኒየራቸውን መሰማት አለባቸው ፤ ጥሩ ተጨዋች ስለሆኑ ብቻ መቆም የለባቸውም ፤ ሁሌም ምክር መስማት አለባቸው፡፡
አብዛኛው የተጫዋችነት ህይወትህን (ሀዋሳ ፣ ደደቢት ፣ ብሄራዊ ቡድን) በአምበልነት አሳልፈሃል፡፡ ይህም ተፈጥሯዊ መሪ እንደሆንክ ያሳያል ፣ ብዙዎች እንደ አርአያ ይመለከቱሃል፡፡ እነዚህ ተደማምረው በምርጥ አሰልጣኝነት በቅርቡ እንደምትመለስ እንጠብቅ?
ክለቦች በኔ ላይ እምነት እስካላቸው ድረስ ወደዚህ ሙያ ብገባ ደስ ይለኛል፡፡ ካቆምኩበት ቀጥዬ ወደ አሰልጣኝነት ብገባ ጥሩ ነው፡፡ ባይሆንም ግን በአሰልጣኝነት የምመለስበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ የቢ ላይሰስ አለኝ ፤ ስለዚህ ከኔ የሚጠበቀው ለአሰልጣኝነት የሚያስፈልጉትን ይዞ መጠባበቅ ነው፡፡