​ሶስት ኢትዮጵያዊያን በካፍ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ አባል ሆኑ

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ከ2010-2012 ድረስ በዘጠኝ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ የተሰየሙ አባላትን ዛሬ ይፋ ሲደርግ ሶስት ኢትዮጵያዊያን በኮሚቴዎቹ ውስጥ የመካተት እድልን አግኝተዋል፡፡

ለሁለተኛ ተከታታይ ግዜ ድሬዳዋን ወክለው በጥቅምት 30 የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንትን የሚወዳደሩት የወቅቱ ፕሬዝደንት ጁኒይዲ ባሻ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ሆነዋል፡፡ ጁኒይዲ በሚገኙበት በዚህ ኮሚቴ የናይጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አማጁ ፒኒክ በፕሬዝደንትነት ሲመሩት፣ ዳኒ ጆርዳን (ደቡብ አፍሪካ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት እና ፍሊፕ ቺያንጉዋ (ዚምባቡዌ) ምክትል ፕሬዝደንት ሆነዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማህበር የቦርድ ፕሬዝደንት አብነት ገብረመስቀል በኢሳ ሃያቱ ዘመን የነበራቸውን የክለብ ውድድሮች እና የክለብ ፍቃድ አዘጋጅ ኮሚቴ አባልነት ዳግም አግኝተዋል፡፡ የዚሁ ኮሚቴ መሪ ቱኒዚያዊው ታሬክ ቦቻማኢ ሲሆኑ አህመድ ያያ (ሞሪታንያ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት እንዲሁም ዳክተር ሙታሲም ጋፍር (ሱዳን) ምክትል ፕሬዝደነት ሆነዋል፡፡

በሴቶች እግርኳስ አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ የፌድሬሽኑ ምክትል ዋና ፀሃፊ መስከረም ታደሰ በአባልነት ተካታለች፡፡ የፊፋ ማስተር ተመራቂ የሆነችው መስከረም ካፍ በሞሮኮ መዲና ራባት በመጋቢት ወር በሚያዘጋጀው የአፍሪካ የሴቶች እግርኳስ ሲምፖዚየም አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ መካተቷ ይታወሳል፡፡ የሴራሊዮን እግርኳስ ማህበር አለቃ እና የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል ኢሳ ጆንሰን የኮሚቴው ፕሬዝደንት ስትሆን የፊፋ ስራ አስፈፃሚ አባል ሊዲያ ንስከራ (ቡሩንዲ) ምክትል ፕሬዝደነት ሆነዋል፡፡

ካፍ በቋሚ ኮሜቴዎቹ ውስጥ የቀደሞ ታዋቂ የአህጉሪቱ ኮከብ ተጫዋቾችን ሲያካትት ከነዚህም መካከል የጋናው ኮከብ አቢዲ ፔሌ፣ የሞሮኮው ሙስጠፋ ሃጂ የአፍሪካ ከ17፣ ከ20 እና ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት ፣ የሴኔጋሉ ካሊሉ ፋዲጋ እና የካሜሮኑ ጀርሚ ጂታፕ የቀድሞ የዛምቢያ ኮከብ ካሉሻ ብዋሊያ በሚመራው የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴ ውስጥ ተካተዋል፡፡ አህመድ አህመድ በአብዛኞቹ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ ወደ ስልጣን ለመምጣት የረዷቸውን ቁልፍ ደጋፊዎቻቸውን በሚያስደስት መልኩ በአባልነት ተካተዋል፡፡

ከድህረ ይድነቃቸው ተሰማ በኃላ ኢትዮጵያዊያን በካፍ እና ፊፋ ያላቸው ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከዓመት ዓመት ወርዷል፡፡ እስከቅርብ ግዜ ካፍን ለሶስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ግዜ የመሩት የካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱ አማካሪ ከነበሩት አንጋፋው ጋዜጠና ፍቅሩ ኪዳኔ ውጪም ኢትዮጵያዊን በካፍ ያላቸው ተሰሚነት እጅጉን ቀንሷል ማለት ይቻላል፡፡ ቋንቋ በተለይም እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ፣ እውቀት፣ የአመራርነት ብቃት እንዲሁም እራስን በደንብ የመግለፅ ችሎታ ያላቸውን የእግርኳስ ባለሙያዎች በሃገራችን እግርኳስ ላይ አለመኖራቸው ኢትዮጵያ በካፍ ያላትን ተፅዕኖ አሳጥቷታል የሚሉ ሃሳቦች በስፋት ይንሸራሸራሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *