ከውበቱ አባተ ጋር ከተለያዩ በኋላ ያለአሰልጣኝ የቆዩት ሀይቆቹ ዋና እና ምክትል አሰልጣኞቻቸውን መርጠዋል።
በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ለመሳተፍ ተገዶ የነበረው ሀዋሳ ከተማ በሊጉ መቆየቱን ቢያረጋግጥም ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር መለያየቱ ግን አልቀረም። በእስካሁኑ የዝውውር ሂደት ውስጥም ክለቡ ዝምታን መርጦ በመቆየት የአሰልጣኝ ሹመትን የመጀመሪያ እርምጃው አድርጓል። ሀዋሳዎች ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንዲመራላቸው ምርጫቸው ያደረጉትም ከዚህ በፊት ከክለቡ ጋር ብዙ ታሪክ ያለውን እና ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት በወልቂጤ ከተማ ያሳለፈው አሰልጣኝ አዲሴ ካሳን ነው።
አሰልጣኝ አዲሴ በተጫዋችነት ዘመኑ በሀዋሳ ከተማ እና ህንፃ ኮንስራክሽን ያሳለፈ ሲሆን በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ከገብረመድህን ኃይሌ እና ሙሉጌታ ከበደ ጋር በመሆን በአማካይ ስፍራ ላይ ተጫውቷል። በ1984 በሀዋሳ እርሻ ቀጥሎም በህንፃ ኮንስትራክሽን ከተጨዋችነት ጋር የአሰልጣኝነትን ስራ የጀመረው አዲሴ ከ1993 ጀምሮ ባሉት አመታት በሀዋሳ ከተማ ከአሰልጣኝ ታመነ ይርዳው እና ከማል አህመድ ጋር በመሆን እስከ 2001 ድረስ በምክትልነት አብሮ መስራት ችሏል። በነዚህ ጊዜያት ዋና አሰልጣኞቹ ባልነበሩባቸው ወቅቶች ክለቡን በራሱ በማሰልጠንም አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከሀዋሳ ከለቀቀ በኋላ 2002 ላይ ደቡብ ፖሊስን ለአንድ አመት ያሰለጠነው አሰልጣኙ 2006 ላይ የሀዋሳን ሁለተኛ ቡድን ይዞ በመቆየት ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በዋናው ቡድን በመምጣት ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር እስከ 2008 አጋማሽ ድረስ መቆየት ችሏል።
ሀዋሳ ከተማ በ1996 እና 1999 የሊጉ ቻምፒዮን እንዲሁም በ1997 የጥሎ ማለፉ አሸናፊ ሲሆን በምክትልነት የቡድኑ አባል የነበረው አሰልጣኝ አዲሴ ሀዋሳ በ2003 በሊጉ 3ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ፣ በ2007 ጥሎማለፍ ለፍፃሜ ሲደርስ እና የ2008 የሲቲ ካፕ ድል ባለድል ሲሆን በተመሳሳይ የምክትል አሰልጣኝነት ሚና ነበረው። አሰልጣኙ አዲሱን ኃላፊነቱን በተመለከተ ያለውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል።
” ክለቡ ላለፉት አመታት በደረጃ በጣም ዝቅ ብሎ እና ብዙ የግብ ዕዳዎችን ይዞ መጨረሱ ቁጭት ፈጥሮብኛል። እኔ በክለቡ ውጤታማ ጊዜያት ላይ ሁሉ አብሬ የነበርኩ በመሆኑ የራሴ አስተዋፅኦ አለ ብዬ አስባለው። በወቅቱ ቡድኑን የመያዝ ዕድል ባገኘሁባቸው ጊዜያት ያቀድኳቸው ነገሮች ተሳክተዋል። አሁንም ቡድኑ ከተረከብኩ በኋላ ያሉበትን ችግሮች በመለየት እንደማሻሽለው አምናለው።”
አዲሴ ካሳ በምክትል አሰልጣኝነት የሚሰራውን ግለሰብ እንዲመርጥ በተሰጠው እድል መሰረት የመረጠው ደግሞ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ነው። ተመስገን የሀዋሳ ከተማን የ17 ዓመት በታች ቡድን እስከ 2008 ድረስ ያሰለጠነ ሲሆን በ2009 እና 2010 ደግሞ የ20 ዓመት በታች ቡድኑን ይዞ ቆይቷል። አሰልጣኙ በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆኑ ይታወቃል።