የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገበትን፣ ጅማ አባ ጅፋር ለመለያ ጨዋታ ያለፈበትን፣ ሻሸመኔ ከተማ ወደ አንደኛ ሊግ የወረደበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ደቡብ ፖሊስ 3-0 ድሬዳዋ ፖሊስ
ደቡብ ፖሊስ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ድሬዳዋ ፖሊስ በሊጉ ለመቆየት የነበራቸውን ህልም ለማሳካት እጅግ ወሳኝ በነበረው ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ በማሸነፍ ከስምንት ዓመታት በኃላ ወደ ሊጉ መግባቱን ድሬዳዋ ፖሊስ ደግሞ ወደ አንደኛ ሊጉ ለመውረድ አፋፍ ላይ የቆመበት ሆኗል።
በሀዋሳ ሰው ሰራሽ የመጫወቻ ሜዳ ላይ የተካሄደው ጨዋታ በሙሉ ክፍለ ጊዜው የባለሜዳው ደቡብ ፖሊስ ብልጫ ነበረበት። ጨዋታው ገና እንደተጀመረ 57ኛው ሰከንድ ላይ ከሚካኤል ለማ ያገኛትን ኳስ በመጠቀም በግምት ከ40 ሜትር ርቀት ላይ ኬኒያዊው አንጋፋ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ አስቆጥሮ ፖሊስን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ አሁንም ለድሬዳዋ ፖሊስ የተከላካይ ክፍል ፈተና ሲሆኑ በተለይ ኤሪክ ሙራንዳ እና ወጣቱ የመስመር ተጨዋች ብሩክ ኤልያስ እጀግ አመርቂ እንቅስቃሴን አሳይተዋል። 9ኛው ደቂቃ ላይ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ የሚገኘው ብሩክ ኤልያስ ከኤሪክ ሙራንዳ የተመቻቸለትን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ግብ ክልል እየገፋ ገብቶ ሁለተኛ ግብ ለደቡብ ፖሊስ አስቆጥሯል፡፡ ድሬዳዋ ፖሊሶች 18ኛ ደቂቃ ገደማ እዩኤል ሳሙኤል ያሻገራትን ኳስ ዘርአይ ገ/ስላሴ ሞክሯት ከወጣችበት ውጭ አንድም የጠራ አጋጣሚን መፍጠር አልቻሉም። 17ኛው ደቂቃ ላይ አየለ ተስፋዬ በቀኝ መስመር በረጅሙ ያሳለፈውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ደቡብ ፖሊስ 3-0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ አሁንም ብልጫን ያሳዩት ደቡብ ፖሊሶች የነበሩ ቢሆንም ድሬዎች ተጨማሪ ግብ እንዳይቆጠርባቸው የኃላ በራቸውን መዝጋት የቻሉበት አጋጣሚ አስገራሚ ነበር። ሆኖም ደቡብ ፖሊሶች በሚካኤል ለማ ፣ ኤሪክ ሙራንዳ፣ ብሩክ ኤልያስ እና በሀይሉ ወገኔ አማካኝነት ዕድሎችን መፍጠራቸው አልቀረም። የጨዋታው የመጨረሻ ውጤት ግን ከእረፍት በፊት በተቆጠሩት ግቦች በባለሜዳዎቹ 3-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር፡፡
ሀዲያ ሆሳዕናን በ2007 ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድገው የነበሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በ1996 ተመስርቶ በ1999 ወደ ፕሪሚየር ሊግ አድጎ 2002 ከሊጉ የወረደው ደቡብ ፖሊስን ከ8 አመት በኃላ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ አስችለዋል፡፡
ሀዲያ ሆሳዕና 1-3 ጅማ አባቡና
በተመሳሳይ 4፡00 በሆሳዕና አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሀድያ ሆሳዕናን ከጅማ አባጅፋር ያገናኘው ይህ ጨዋታ በቀጥታ ሊጉን ለመቀላቀል ለአባቡና አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም ደቡብ ፖሊስ በማሸነፉ ምክንያት የምዕራቡ ቡድን ጨዋታውን 3-1 ቢረታም ምድብ ለን ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጭነው መጫወት የቻሉት አባቡናዎች ሱረፌል ጌታቸው በ9ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ እየመሩ ነበር ወደ እረፍት ያመሩት።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀድያ ሆስዕናዎች በ53ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወ/ዮሀንስ ጎል አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ዳግም ወደ ጨዋታው የተመለሱት ጅማ አባ ቡናዎች በ64ኛ ደቂቃ በከፍተኛ ሊጉ ግብ አስቆጣሪ ብዙዓየሁ እንደሻው አማካኝነት በድጋሚ መሪ ሲሆኑ በ87ኛ ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታደሰ ሶስተኛዋን ግብ ለአባቡና አክሎ ጨዋታው በጅማ አባ ቡና 3-1 አሸነፊነት ተደምድሟል። በዚህም መሰረት ጅማ አባቡና ምድብ ለን ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ሽሬ እንደስላሴን ድሬዳዋ ላይ ነሀሴ 26 የሚገጥም ይሆናል፡፡
ቡታጅራ ከተማ 3-2 ካፋ ቡና
ቡታጅራ ከተማ ከፉ ቡናን በሜዳው በገጠመበት ጨዋታ በተነሳ ረብሻ ቡታጅራ በፌድሬሽኑ ሜዳው በመቀጣቱ ምክንያት ሀዋሳ ላይ ጨዋታውን ለማድረግ ተገዷል። ሀላባ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ ካደረጉት ጨዋታ በኃላ በደቡብ ኮሌጅ ሜዳ በጀመረው በዚህ ጨዋታ ቡታጅራ ከተማ አሸንፎ በከፍተኛ ሊግ መቆየቱን አረጋግጧል። የቡታጅራን መሸነፍ ይጠብቅ የነበረው ሻሸመኔ ከተማ ደግሞ አንድ ጨዋታ እየቀረው ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል። በጨዋታው 16ኛው ደቂቃ ላይ ቀነኒ አብዱላዚዝ እንዲሁም በ21ኛው ደቂቃ ደግሞ አቡበከር ወንድሙ ግብ አስቆጥረው ከፋን ቀዳሚ አድርገዋል። ቡታጅራዎች በአንፃሩ ክንዴ አብቹ እና ኤፍሬም ቶማስ በ25 እና 35ኛ ደቂቃዎች አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ መስቀሌ መንግስቱ በቀኝ በኩል በረጅሙ የላከለትን ኳስ ክንዴ አብቹ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛና ወሳኝ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በቡታጅራ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ሀላባ ዘንድሮም አልተሳካለትም
ወልቂጤ ከተማ በፌዴሬሽኑ በተጣለበት ቅጣት ምክንያት ሀዋሳ ላይ ከሀላባ ከተማ ባደረገው ጨዋታ ሀላባ ከተማ በስንታየሁ መንግስቱ ጎሎች ታግዞ 2-1 አሸንፏል። ሆኖም ደቡብ ፖሊስ እና ጅማ አባ ቡና በተመሳሳይ ባለማሸነፋቸው የሀላባ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመግባት ህልም ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት ተጨናግፏል።
በሌላ የዛሬ ጨዋታ ወደ መቂ አምርቶ አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው መቂ ከተማን የገጠመው ሀምበሪቾ በቴዲ ታደሰ እና ፍፁም ታደሰ ጎሎች 2-1 አሸንፏል።
የደረጃ ሰንጠረዥ