Soccer Ethiopia

“አብዛኛው የታዳጊነት ጊዜዬን ከዋናው ቡድን ጋር ማሳለፌ ብዙ ጠቅሞኛል” ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ዋልታ ዓንደይ

Share

የስሑል ሽረው ተስፈኛ ግብ ጠባቂ የዛሬው የተስፈኞች ዓምድ እንግዳችን ነው።

በተቀያሪ ወንበር ላይ በሚያሳያቸው እንቅስቃሴዎች በልዩ ይታወቃል። ቡድኑ የግብ እድሎች ሲያመክን ይቁነጠነጣል፤ በተጨማሪ ደቂቃዎችም ለቡድኑ ኳሶችን ለማቀበል ወዲያ ወዲህ ይላል። ለአሳዳጊ ክለቡ ልዩ ፍቅር እንዳለው የሚገልፀው የዛሬ እንግዳችን ዋልታ ዓንደይ ተሰልፎ በተጫወተባቸው ጥቂት ጨዋታዎችም ተስፋ ያለው ግብ ጠባቂ እንደሆነ አስመስክሯል። በሽረ እንዳሥላሴ ተወልዶ በከተማዋ እግርኳስን መጫወት የጀመረው ይህ ግብ ጠባቂ በታዳጊ ቡድን ደረጃ ለካባ ወያነ ከተጫወተ በኃላ ብዙም ሳይቆይ ነው ወደ ከተማው ትልቅ ክለብ ስሑል ሽረ የተቀላቀለው።

ከ2008 ጀምሮ ታዳጊ እያለ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ መስራት ጀምሮ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ዋልታ ምንም እንኳ ከፊቱ በሊጉ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ ግብጠባቂዎች ውስጥ የሆኑት ምንተስኖት አሎ እና ወንድወሰን አሸናፊ ቢገኙም በቀጣይ ዓመታት የስሑል ሽረ ግብ የመጠበቅ ህልም እንዳለው በልበ ሙሉነት ይናገራል።

ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ቆይታ እነሆ..

“እግር ኳስ እንደ ማንም ኢትዮጵያዊ በሰፈር ነው የጀመርኩት። ከዛ በኃላ ‘ ካባ ወያነ ‘ ወደሚባል ቡድን ገባሁ እዛ የብዙ ጊዜ ቆይታ አልነበረኝም። ወደ ሽረ ሁለተኛ ቡድን የገባሁትም በአጋጣሚ ነው። አንድ ቀን ሚካኤል ሲሳይ የሚባል የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ (በአሁን ወቅት በመቐለ 70 እንደርታ ነው ያለው) መንገድ ላይ የግብ ጠባቂ ማልያ አድርጌ የቀን ስራ ስሰራ አየኝ ፤ ከዛ የግብ ጠባቂ ማልያ አድርጌ የቀን ስራ መስራቴ ትኩረቱን ሳበው መሰለኝ መጥቶ አነጋገረኝ። ትጥቄን አድርጌ ወደ ሜዳ እንድመጣ ነገረኝ። እኔም ባለኝ ቀን ወደ ልምምድ ቦታ ሄድኩ። ወደ እግር ኳስ የገባሁበት አጋጣሚ ይሄ ይመስላል።

“በሽረ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ በቢጫ ቴሴራ ብዙ ጊዜ ነው የቆየሁት። አብዛኛው የታዳጊነት ጊዜዬ ከዋናው ቡድን ጋር ነው ያሳለፍኩት። ይሄም ብዙ ጠቅሞኛል። በ2010 በግል ጉዳይ ከእግር ኳሱ ለመራቅ ከተገደድኩበት ወቅት ውጭ በአረንጓዴ ቴሴራ ወደ ዋናው ቡድን እስካደግኩበት 2012 በሽረ ያለኝ ቆይታ አሪፍ ነው። ዘንድሮ ብዙ ልምድ የወሰድኩበት ራሴን ለማሻሻል ጠንክሬ የሰራሁበት ዓመት ነበር። የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታም አድርጌያለሁ። ከድሬዳዋ ጋር ስንጫወት በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወንድወሰን አሸናፊ በቀይ ሲወጣ እሱን ተክቼ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ግቤን ሳላስደፍር ወጥቻለው። ጨዋታው የመጀመርያዬ ስለነበር ትንሽ ስሜታዊ ሆኜ ነበር። በጨዋታው ግን ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ብቃት ነው ያሳየሁት። ቡድናችን ውጤቱን ይዞ እንዲወጣ ጥሩ ድርሻ ነበረኝ።

“በቀጣይ ብዙ ነገሮች የመስራት እቅድ አለኝ። አሳዳጊ ክለቤ ስሑል ሽረን ለረጅም ዓመታት ማገልገል እፈልጋለው፤ የሚኖር ታሪክ መስራት እፈልጋለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top