የዳኞች ገፅ | ታታሪው “ኤሊት ኤ” ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል

ከአዲሱ ሚሌኒየም ወዲህ በኢትዮጵያ ዳኝነት ከተመለከትናቸው ምስጉን ዳኞች መካከል ይመደባል። ለሙያው የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው ኤሊት ኤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

እግርኳስን ተጫዋች ለመሆን የነበረው ከፍተኛ ፍላጎት ረጅም ርቀት ባያስኬደውም በአጋጣሚ ፊቱን ወደ ዳኝነቱ በማዞር ቀስበቀስ አንቱታን በማትረፍ ስኬታማ መሆን ችሏል። ከመምሪያ የጀመረው የዳኝነት ህይወቱ እጅግ በሚያስገርም ፍጥነት ወደ ላይ ተመንጥቆ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብቸኛው ኤሊት ኤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ እንዲሆን አስችሎታል። እጅግ የተረጋጋ፣ ለመናገር በጣም ቁጥብ እና ሙያውን አክባሪ መልካም ሰው እንደሆነ የሚነገርለት ተመስገን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልልቅ የሚባሉ ጨዋታዎችን በብቃት እየዳኘ ከመገኘቱ ባሻገር በአህጉራዊ መድረክም የተለያዩ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ውድድሮችን በመምራት ከበዓምላክ ተሰማ ጋር በመሆን የሀገሩን ስም እያስጠራ ይገኛል። ወደፊትም ካፍ እና ፊፋ ከፍተኛ እምነት ጥለውበት ትልልቅ ውድድሮችን ይመራል ተብሎ ይጠበቃል። የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን የሆነው ኤሊት ኤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል ስላሳለፈው የዳኝነት ህይወቱ እና ከፊቱ ስለሚጠብቁት በጎ ነገሮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ!

ትውልድህ የት ነው? ወደ ዳኝነቱስ እንዴት ልትገባ ቻልክ?

ትውልዴ ከደብረብርሃን አለፍ ብላ በምትገኘው ደብረ ሲና ከተማ ነው። ወደ ደብረ ብርሀን በመምጣት በምኖርበት አካባቢ ስታዲየም በአቅራቢያዬ ይገኝ ነበር። በልጅነቴም ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው ስታዲየም ውስጥ ነበር። እዚሁ የስፖርት ኮሚሽን ሜዳ ላይ ልምምድ ሰርተን፣ ተጫውተን ከዛ ልጆችን ጨዋታ እናጫውት ነበር። እኛ እዛ ስንሰራ ደግሞ እነ ፀጋዬ ከበደ እና ሲያምረኝ ዳኜን እንመለከት ነበር። በዋናነት ግን በልጅነቴ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ታቅፌ እግርኳስ እጫወት ነበር። ከዛም እዛው ሜዳ የማሳልፈው ጊዜ ስለበዛ እየተጫወትኩ እንዲሁም ጨዋታዎችን እያጫወትኩ ወደ ዳኝነቱ ቀስ በቀስ ገባሁ።

በእግርኳስ ተጫዋችነት እስከምን ድረስ ተጓዝክ?

እግርኳስን በፕሮጀክት ደረጃ ለሰሜን ሸዋ ዞን ተጫዋቻለሁ። በመቀጠልም ለደብረ ብርሃን ከተማ ግልጋሎት ሰጥቻለሁ። በተጨማሪም ደብረ ብርሃን ፖሊስ ለሚባል ክለብ ተጫውቻለሁ። በእግርኳስ ህይወቴም ግብ ጠባቂ ነበርኩ።

የመጀመሪያ የዳኝነት ትምህርትህን መቼ ወሰድክ?

መምሪያ ሁለትን ከወሰድኩ ቆየት ብሏል። በጊዜው ኢንስትራክተር ተስፋዬ ለገሰ ናቸው ስልጠናውን የሰጡኝ። ከዛም ይህንን የመምሪያ ሁለት ፍቃድ ይዤ ለረጅም ጊዜያት ካገለገልኩ በኋላ የፌዴራል ደረጃ ትምህርቴን ተከታተልኩ። በመሐል መምሪያ አንድ የሚባል አለ። ግን መምሪያ ሁለትን ከወሰድክ በኋላ ለአራት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠህ መምሪያ አንድን እንደያዝክ ይቆጠራል። እኔም ዳኝነት ውስጥ በደንብ ሳልገባ እግርኳስ ተጫዋች ሆኜ ነበር መምሪያ ሁለትን የወሰድኩት። ወደ ዳኝነቱም ከገባሁ በኋላ እስከ 1999 በመምሪያ ሁለት ግልጋሎት ከሰጠሁ በኋላ በ1999 መጨረሻ ላይ የፌዴራል ትምህርቴን ወሰድኩ። ትምህርቱንም ሻለቃ በልሁ ሰጥተውኝ 2000 ላይ የፌዴራል ዳኛ ሆኛለሁ። እንደውም በትምህርቱ ጥሩ ብቃት በማሳየቴ እና አንደኛ በመውጣቴ ሻለቃ በልሁ ሽልማት ሰጥተውኛል።

የፌዴራል ዳኛ ሆነህ የመጀመሪያ ጨዋታህን ታስታውሳለህ?

2000 ላይ የፌዴራል ዳኝነት ፍቃዳችን ሊመጣ ሲል ፌዴሬሽኑ ጋር ጥሩ ነገር አልነበረም ነበር። የፌዴሬሽን እና የክለቦች ኅብረት የሚባል ጎራም በሀገሪቱ ተፈጥሮ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የፌዴራል ትምህርቱን የሰጡኝ ሻለቃ በልሁ ወደ ክለቦች ኅብረት ያዘነብሉ ነበር። ከዛ በጊዜው ደውለውልኝ ‘ዳኝነት መስራት ከፈለግክ እኛ ጋር ና። ክለቦች ለብቻቸው አሉ። ስለዚህ እዚህ መጥተህ አጫውት’ አሉኝ። እኔም መሥራት ስለምፈልግ ወዲያው እሺ ብዬ ነው የሄድኩት። የሚገርምህ የመጀመሪያ ጨዋታዬ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ነበር። እኔ ግን ስታዲየሙን ስለማላቀው በስህተት ጃን ሜዳ ነበር የሄድኩት (እየሳቀ)። እንደገና ስልክ ደውዬ ቦታውን ጠይቄ ነው በድጋሚ ወደ አበበ ቢቂላ የሄድኩት። ብቻ እንደምንም ስታዲየም ደረስኩ። ደግሞ የመጀመሪያ ጨዋታዬን በፕሪምየር ሊግ ነበር የጀመርኩት። ሻሸመኔ ከተማ እና ኒያላ ያደረጉትን ግጥሚያ ነበር በረዳት ዳኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በፌዴራል ዳኝነት የመራሁት። ከዛም 25 ክለቦች በሊጉ እንዲጫወቱ ሲወሰን እና መግባባት ላይ ሲደረስም በቋሚነት ማገልገሌን ቀጠልኩ።

የፈተነህ ጨዋታ…?

ፌዴራል ዳኛ ሆኜ የማልረሳው ጨዋታ 2004 ላይ የተደረገው የደደቢት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ነው። ጨዋታው ከባድ ግምት የሚሰጠው ነበር። ከዛ በጨዋታው ላይ ጥሩ እያጫወትኩ ስሮጥ ማራገቢያው ከእጄ የወደቀብኝን አጋጣሚ መቼም አልረሳውም።

ፌዴራል ከሆንክ በኋላ ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆንከው በፍጥነት ነው። በምን ምክንያት ነው በአጭር ጊዜ ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆንከው?

ልክ ነው! 2000 ላይ ፌዴራል ከሆንኩ በኋላ አራት ዓመታት ብቻ ሰርቼ 2005 ላይ ኢንተርናሽናል ዳኛ የሆንኩት። እንዳልከው ፈጥኗል፤ ግን ከዳኝነቱ በፊት እግርኳስ እጫወት ስለነበረ ብዙ ነገሮቹ ይገቡኛል። በተጨማሪም ፌዴራል ስሆን ወዲያው ፕሪምየር ሊጉን ማጫወቴ እና ጎበዝ ተብዬ መሸለሜ የበለጠ እንድጠነክር አነሳስቶኛል። ከዚህ መነሻነት ልምምዴን ቀን በቀን በደንብ በመስራት ራሴን ማብቃት ያዝኩ። ራሴንም በደንብ ስለማበቃ ጥሩ ጥሩ ጨዋታዎች ላይ እመደብ ጀመር። 2004 ላይ ካርሎስ የሚባል ግለሰብ ሃገራችን መጥቶ ትምህርት ይሰጥ ነበር። በጊዜው ‘ወደፊት ኢንተርናሽናል ይሆናሉ የምትሏቸውን ዳኞች አምጡ’ ሲል እኔ፣ ትግል፣ ኃይለየሱስ፣ አበራ እና ሌሎችንም በጊዜው ጥሩ ብቃት ላይ የነበርነውን 4 ዋና እና 4 ረዳት ዳኞች ስም ለእርሱ ሰጡ። ከዛ ትምህርቱ ላይም ተካፍለን የሚቀጥለው ኤሊት ውስጥ ገብተን እሱ ሄደ። በጊዜው ትምህርቱን ወስደው ነገር። ግን በተለያዩ ምክንያቶች ፈተናውን በወደቁት ምትክ ትግል እና ኃይለየሱስ በምትኩ ገቡ። በሚቀጥለው ደግሞ አንድ ሰው ሲወጣ እኔን በወጣው ሰው ተተካሁ።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነህ መጀመሪያ ያጫወትከውን የመጀመሪያ ጨዋታ ታስታውሰዋለህ?

በነገራችን ላይ ኢንተርናሽናል ዳኛ መሆኔን የሚገልፅ ባጅ የተቀበልኩ ዕለት ኢትዮጵያ እና ሱዳን የወዳጅነት ጨዋታ ነበራቸው። አዲስ አበባ ላይ የተደረገውን ይህንን ጨዋታ መርቻለሁ። ከዛ በመቀጠል ይህንን ጨዋታ በመራሁ በ15ኛው ቀን ወደ ሩዋንዳ ተጓዝኩ። ጨዋታው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ነበር። እሱን ጨዋታ ለመዳኘት ከበዓምላክ እና ክንዴ ጋር ተጓዝን። ስለዚህ ከወዳጅነት ጨዋታው ውጪ በኢንተርናሽናል ደረጃ መጀመሪያ ያጫወትኩት ሩዋንዳ ሄጄ ነው። እንግዲህ ከ2005 ጀምሮም እስካሁን ድረስ ሳላቋርጥ በኢንተርናሽናል ዳኛነት እያገለገልኩ እገኛለሁ።

በዳኝነት ዘመንህ ያገኘሃቸው የኮከብነት ሽልማቶችን ንገረኝ ?

2004 ላይ በፌዴራል ዳኛነት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እያጫወትኩ ምስጉን ረዳት ዳኛ ሆኜ ተሸልሜያለሁ። በጊዜው ምስጉን ዋና ዳኛ የነበረው ኃይለየሱስ ባዘዘው ነበር። በመቀጠልም ደግሞ 2010 ላይ ቴዎድሮስ ምትኩ ዋና ሲባል እኔ ምስጉን ረዳት ዳኛ ተብዬ በድጋሚ ተሸልሜያለሁ።

ኢንተርናሽናል ኤ ረዳት ዳኛ ከሚባሉት የአህጉራችን ምርጥ ረዳት ዳኞች ውስጥ አንዱ አንተ ነህ። በሃገራችንም በዚህ ደረጃ ያለህ አንተ ብቻ ነህ። ይህንን ማዕረግ መቼ አገኘከው?

ካፍ በየደረጃው የሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ስልጠናዎች አሉ። እኔም 2005 ላይ ኢንተርናሽናል ዳኛ ስሆን ያንግ ታለንት ኮርስ ለመውሰድ ከኢትዮጵያ ተመርጬ የወሰድኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። በቀጣይ ዓመትም ይህንኑ ኮርስ እኔው ራሴ ሄጄ ወሰድኩ። 2007 እና 2008 ላይ ደግሞ በደረጃ ኤሊት ቢ የሚባለውን ኮርስ ግብፅ እና ካሜሩን ላይ ለሁለት ዓመት ወሰድኩ። ከዛም ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ያንን ሁሉ ትምህርት ወስጄ እዚህ ደረጃ ላይ ደረስኩ። ግብፅ ላይ የተደረገውንም የአፍሪካ ዋንጫ በረዳት ዳኝነት እንዳገለግል ተመርጬ ሄጃለሁ። ይህ የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያዬ ነበር። እርግጥ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫን 2015 እና 2017 ላይ ለመምራት ኒጀር እና ጋቦን ሄጃለው። ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫንም ለመምራት 2018/19 ላይ በድጋሚ ኒጀር ተጉዤ አጫውቻለሁ።

እንዳልከኝ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ጥሩ ተሳትፎ ነበረህ። በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ላይ የመራኸው ትልቁ ጨዋታህ የቱ ነው?

2018 መጨረሻ ላይ አል-አህሊ ከ ኢ ኤስ ሴቲፍ ያደረጉት ትልቅ ግምት ያገኘ እና ከባድ ግጥሚያ ነበር። ይህንንም ጨዋታ ከበዓምላክ፣ ክንዴ እና በላይ ጋር በመሆን ነበር የመራነው።

ጠንካራ ጎኔ ምንድን ነው ትላለህ?

ለሙያው ስል ምንም ነገር ወደ ኋላ እላለው። ለሙያው ማንኛውንም ነገር መስዋዕት አደርጋለው። ቅድም እንደገለፅኩልህም ልምምዴን በደንብ ነው የምሰራው። በሳምንት ሦስቴ ወይም አራቴ አደለም ልምምድ የምሰራው። በየቀኑ ነው ልምምድ የማደርገው። ከዚህ በተረፈ ጨዋታዎቸን በደንብ አያለው። ጨዋታዎች ላይም ትክክለኛ ፍርድ እሰጣለሁ። ከህሊናዬ ጋር ሳልጣላ አቅሜ የፈቀደውን ነገር ሜዳ ላይ አደርጋለሁ። በተጨማሪም ሙያው የማይፈልጋቸውን ነገሮች ከራሴ አስወግዳለው። ከእነዚህ ውጪ ፈጣሪዬ እንዲያግዘኝ ፀሎት አደርጋለሁ። የፈጣሪዬም እርዳታ ተጨምሮበት ነው እዚህ የደረስኩት።

ብቸኛው የሀገራችን ኤሊት ኤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ በመሆንህ ምን ይሰማሃል?

እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ነገሮችን አልፌያለሁ። ምንም ጊዜው አጭር ቢመስልም በውስጡ ከባድ ነገሮችን አሳልፌያለሁ። ተመርጠህ ከሄድክ በኋላ እዛ ብዙ ፈተናዎች ይጠብቁሃል። ብቻ በአጠቃላይ ጥሩ እና መጥፎ ነገሮችን አሳልፌ ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት። ሲጀምር አሁን የደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ የሆነው በዓምላን ከአጠገቤ ስለሆነ ነው። የትም ስሄድ የበዐዓምላክ ረዳት መሆኔን ሲያቁ ነው ለእኔ ትልቅ ነገር የሚኖራቸው። ባምላክ ትልቅ ስም ስላለው ይህ ስም ለእኔ በጣም በትልቁ ጠቅሞኛል። ራሴን እንዳጎለብት እና ጠንካራ ሰራተኛ እንድሆንም ባዓምላክ ረድቶኛል። በዳኝነቱም ሃገራችን ትልቅ ስም እንዲኖራት ባዓምላክ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ስለዚህ በዓምላክ እኔንም ጠቅሞኛል። በተጨማሪም የሙያ አጋሮቼ ጨዋታ ስመራ የነበረኝን ብቃት እንዲሁም ክፍተት ይነግሩኛል። ይህ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል?

ባለትዳር ነኝ። በተጨማሪም የ7 እና የ3 ዓመት ወንድ ልጆች አባት ነኝ። ባለቤቴም በዚህ የዳኝነት ሙያዬ በደንብ ታግዘኛለች። እኔ ለሌት ተነስቼ ወደ ልምምድ ስሄድ እሷም ለእኔ የሚጠቅሙ ነገሮችን ለማዘጋጀት ትለፋለች። በአጠቃላይ ከቤተሰብ የማገኘው እገዛ እና ሠላም ለእኔ ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል።

አሁን በሃገራችን ያለው የዳኝነት ደረጃ ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ነው የምታስበው?

እውነት ለመናገር በሃገራችን ያለው የዳኝነት ደረጃ የተሻለ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ከበፊቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳለ ይሰማኛል። ጥሩ ጥሩ አዳዲስ ዳኞችም እየመጡ ነው ያሉት። ስለዚህ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ እና ወደፊት የበለጠ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚሆን ተስፋ ሰጪ ነገሮች እንዳሉበት አስባለው። ሁሉም ዳኛ ነገን እያሰበ ስለሚለፋ ጥሩ ደረጃ ላይ እንገኛለን።

ዳኛ ለመሆን ለሚያስቡ ሰዎች ምን ምክር ትለግሳለህ?

በተፈጥሮ ዳኝነት ንፁህ ልብ እና ህሊና ይፈልጋል። በተጨማሪም ታማኝ መሆንን ይሻል። በዚህ ሙያ ውስጥ ካለህ እስከ ምትሞት ድረስ ታማኝ መሆን አለብህ። ስለዚህ ለእውነት መስራት ከምንም በላይ ወሳኝ ነው። ከዚህ በተረፈ ራስን ምን ጊዜም ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ልምምድን መስራት እንዲሁም ራስን የሚያሳድጉ ነገሮችን ማንበብ እና መከታተል ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ግን ሙያውን ሙያዬ ብሎ ማክበር እና መገዛት ያስፈልጋል።

የወደፊት እቅድህ ምንድን ነው?

ዳኛም ልክ እንደ ተጫዋች አንዳንድ ጊዜ አቋሙ ይወርዳል። እና ዋነኛ እቅዴ አቋሜ ሳይወርድ በጥሩ ብቃት ጨዋታዎችን መምራት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ራሴን ለዓለም ዋንጫ ውድድር ለማብቃት አልማለሁ። ስለዚህ የተሻሉ ጨዋታዎችን በአህጉሪቱ አጫውቼ በቀጣይ የዓለም ዋንጫን ለመምራት እቅድ አለኝ።

የቀለም ትምህርትህን መቀጠል ታስባለህ?

በዚሁ በዳኝነት ፍቅር የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን ሁለት ጊዜ አቋርጫለሁ። አሁን ግን በርቀት እየተማርኩ ስለሆነ ዘንድሮ በዳኝነት ያቋረጥኩትን ትምህርት እጨርሳለሁ። እርግጥ በመጀመሪያ ተምሬ የነበረው መምህርነት ነበር። ከዛም ዘርፉን ቀይሬ በህግ ትምህርት ነበር ስማር የነበረው። በዚህም ፍርድ ቤት የችሎት ድጋፍ ሰጪ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። አሁን ደግሞ በማኔጅመንት ለመመረቅ ወራቶች ብቻ ይቀሩኛል።

አሁን ያለህበት ደረጃ እንድትደርስ የረዱህን ሰዎች ማመስገን የምትፈልግ ከሆነ እድሉን ላመቻች?

በጣም ደስ ይለኛል። እኔ የብዙ ሰዎች ውጤት ነኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ ሲረዱኝ የነበሩ ሰዎች አሉ። በፌዴሬሽን አካባቢም ሲያስተምሩኝ የነበሩ ኢንስትራክተሮች ነበሩ። በተጨማሪም አብረውኝ የሚሰሩ የሙያ ባልደረቦቼ አሉ። ከዚህ ውጪ ደግሞ ደብረብርሃን ብዙ አትሌቶች የሚፈልቁባት ሃገር ስለሆነች ፈተናዎች እና ውድድሮች ሲኖሩብኝ እነሱ ጋር ሄጄ ነበር የምሰራው። ስለዚህ አትሌቶች እና የአትሌት አሠልጣኞችን በተለይ አሰልጣኝ በለጠን መኮንን ማመስገን እፈልጋለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኩክ የለሽ ማርያምን ማመስገን እፈልጋለሁ።



© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!