የጅማ አባጅፋር ቦርድ በአሰልጣኙ ቆይታ እና የውጪ ተጫዋቾች ዙርያ ውሳኔ አሳልፏል

በዛሬው ዕለት የጅማ አባጅፋር የቦርድ አመራር ባደረገው ውይይት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እንዲቀጥሉ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አጃይብ አባሜጫ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ረፋድ ላይ በነበረው የቦርድ አባላት ውይይት ላይ የገንዘብ ችግሮችን ለመፍታት ወጪ የመቀነስ እንዲሁም የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች በቅርቡ መሰራት እንጂምሩ የተወሰነ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ ጊዜ ጀምሮ ክለቡ በርካታ ወጪዎችን በማውጣት የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ሲያመጣ እንደቆየ አውስተው ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ ግን ክለቡ የውጪ ተጫዋቾችን ከመጠቀም ይልቅ በሀገር ውስጥ ባሉ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ለማድረግ ወስኗል። በጅማ እና አካባቢዋ ላይ ያሉ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን በስፋት ለመጠቀም ከድምዳሜ ተደርሷልም ብለዋል፡፡

ሌላው እና ዋናው በአሁኑ ሰዓት ለሰበታ ከተማ ዋና አሰልጣኝነት እየተወዳደሩ የሚገኙት እና አምና ክለቡን በኮቪድ 19 እስኪቋረጥ ሲመሩ የነበሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እንዲቀጥሉ ወስነው መውጣታቸውን አቶ አጃይብ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!