Soccer Ethiopia

አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ የት ይገኛል?

Share

በቅርብ ጊዜያት ከዕይታ የራቁ የእግርኳስ ሰዎችን በምናቀርብበት አምዳችን በኤሌክትሪክ ከተጫዋችነት እስከ አሰልጣኝነት ለረዥም ዓመታት አገልግሎ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከአሰልጣኝነት የራቀው ብርሀኑ ባዩ የት ይገኛል? ስንል ጠይቀናል።

የእግርኳስ ሕይወቱን በ1979 በጭማድ ( ጭነት ማመላለሻ ድርጅት) ጀምሮ በክለቡ አንድ ዓመት ከቆየ በኃላ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አማካኝነት ወደ መብራት ኃይል ተዘዋውሮ ከእግርኳስ እስከ ተገለለበት ጊዜ ድረስ በቀዩ ቤት ቆይታ አድርጓል። በተጫዋችነት ጊዜውም ከክለቡ ጋር በ1985 የኢትዮጵያ ቻምፒዮን እንዲሁም በ1986 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አሸንፋል። በወቅቱም ለወጣት ብሄራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታዎች አድርጓል። በ1987 ከእግር ኳስ ተገልሎ ወደ ድርጅቱ ፅሕፈት ቤት በመቀላቀል ሥራ ከጀመረ በኃላ ጎን ለጎን የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች ወስዶ በአጭር ጊዜ ወደ ስፖርቱ መመለስ ችሏል። በመብራት ኃይል የቴክኒክ ኮሚቴ በመሆን ስራውን ጀምሮ ጥቂት ጊዜያት ከሰራ በኃላም የዮርዳን ስቶይኮቭ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ለአምስት ዓመታት ክለቡን አገልግሏል። ከዛ በኃላም የአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ምክትል ሆኖ ሰርቷል። ከ2007 እስከ 2010 መጀመርያ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ሰርቷል። ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአሰልጣኝነት ሞያው ተለይቶ በተመረቀበት ሌላ ሙያ ተሰማርቶ የሚገኘው አሰልጣኝ ብርሃኑ በወቅታዊ ሁኔታው አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ያደረገው ቆይታን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አሁን በምን ሁኔታ ይገኛል ?

ከእግር ኳሱ ትንሽ ራቅ ብያለው። በአሜሪካ የጀመርኩት አንድ ስልጠና አለ፤ ላሊጋ ሜተዶሎጂ የሚባል ኮርስ ወስጃለው። ከሞያው ብርቅም ራሴን በተለያዩ ነገሮች በማሳደግ ላይ ነኝ።

ከአሰልጣኝነት ሙያ የራቀበት ምክንያት

እውነት ይመስለኛል ያራቀኝ። በእግር ኳሱ ስፖርትን ለማሳደግ የሚሰሩ እንዳሉ ሁሉ በአንፃሩም ለግል ጥቅም የሚሄዱ ግለሰቦችም አሉ። ከነሱ ጋር አብሮ መስራት አስቸጋሪ ነው። ሙስናው ይበዛል። እግር ኳሱ ላይ ብልሹ አሰራር በዝቷል። እውነት ከሌለ መራቅ ይሻላል፤ እውነትና የስራ ሥነ ምግባር እስኪመጣ። አቅም አንሶኝ አይደለም፤ በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመርያ ዲግሪ አለኝ፤ በአካውንቲንግም ዲፕሎማ አለኝ። በእግርኳስ አሰልጣኝነትም በቂ ትምህርት እና ልምድ አለኝ። በዚህ ሰዓት መስራት ነበረብኝ። ግን ከባቢው ተበላሽቷል።

በእግርኳሱ ሰዎችን ከሞያው ለማራቅ የሚደረግ ነገር አለ። አሁን እኔ ከመብራት ኃይል የወጣሁበት መንገድ ደስ አይልም። እርግጥ ነው ቦታው ርስት አይደለም። ውጤት ካለህ ትቆያለህ ካልሆነ መልቀቅ ነው። ግን ስትወጣም አወጣጥህ ደረጃ አለው። እኔ ግን ብዙ ዓመት ከሰራሁበት ቤት ተገፍቼ ነው የወጣሁት። ለክለቡ ብዙ ነገር አድርጌያለው ፤ ዋናው አሰልጣኝ መቶ ሺ ሲያገኝ ቋሚ ሰራተኛ ነው በሚል ሰባት መቶ ሃምሳ ነበር የሚከፈለኝ። ከመብራት ኃይል ከወጣሁ ከጥቂት ወራት በኃላ ስራ አግኝቼ ነበር።

አሁን ያለበት ሁኔታ

ከአሰልጣኝነት ከወጣሁ በኃላ በድርጅታችን አንድ ስልጣና አለ ‘ Training And development ‘ የሚባል ስልጠና እዛ ላይ እየሰራሁ ነው። ከዛ በተጨማሪም ስልጠናው ከስፖርት ጋር የተያያዘ ነገር አለው፤ እዛ ላይም እየሰራሁ ነበር። አሁን ደግሞ አድሚስትሬሽን አሲስታትን ሆኜ እየሰራሁ ነው።

በቀጣይ ወደ አሰልጣኝነት ስለመመለስ

እግርኳስ በውስጤ ያለ ነገር ነው። በትምህርት ረገድ ብናይም በቂ የትምህርት ዝግኝት አለኝ። በሃገር ውስጥ እስከ ኤ ላይሰንስ አለኝ። ከሃገር ውጭም ላ-ሊጋ ፎርሜሽን ሜተዶሎጂ ለሦስት ዓመታት ወስጃለው። ሁኔታዎች ሲመቻቹ እመለሳለሁ። ሌላ አሰልጣኝ ገፍቼ መመለስ ሳይሆን ትክክለኛ የሆነ አሰራር ካለ በርግጠኝነት እመለሳለው። ሞያውን እወደዋለሁ። በመብራት ኃይል እግርኳስ ቡድንም ለማሰልጠን ተመዝግቤያለሁ። ከተሳካ ጥሩ ነው እመለሳለሁ።

በርግጥ ከመብራት ሃይል ከወጣሁ ከወር ምናምን በኃላ ከሌላ ክለብ ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር። ግን የሆነ ያልተስማማሁበት ነገር ነበር፤ ከተስማማሁት ገንዘብ ውጭ የሆኑ ቁጥሮች ተጨምረው እዛ ላይ ፈርምና ገንዘቡን በአንድ ግለሰብ የባንክ ደብተር አስገባ። ከዛ ቡድኑን ተረከብ አሉኝ። ይሄ ደግሞ ከኔ ስብእና ጋር አይሄድም። አልተስማማሁም ስላቸው ከሲስተሙ ትወጣለህ አሉኝ። ከፈለገ እስከመጨረሻው አልመለስ ብዬ ስራውን ተውኩት። ከዛ በኃላም አጋጣሚዎች ነበሩ። ግን ተመሳሳይ ነገሮች ስለነበሯቸው መስራት አልፈለግኩም። ከራሴ ጋር መጣላት አልፈልግም።

በመጨረሻ

እውነት ይኑር። እግር ኳሱን ለማሳደግ ከዚ ነገር እንውጣ። ሁሉም ነገር በግሩፕ በኔትወርክ ነው የሚሰራው። እና ከዚህ ነገር ወጥቶ እግርኳሱ በስርዓት ይመራ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top