Soccer Ethiopia

የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከሱሌይማን ሀሚድ ጋር

Share

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተገኝቶ ራሱን በአዳማ ከተማ ያጎለበተው ሱሌይማን ሀሚድ በዘመናችን ከዋክብት ገፅ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

የዛሬው እንግዳችን ሱሌይማን በቤልሻል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው። እንደ አብዛኞቹ የሃገራችን ታዳጊዎችም በሰፈሩ በሚገኙ የመጫወቻ ሜዳዎች ላይ ከትምህረት ቤት መልስ ያለውን ጊዜ በማሳለፍ ከእግርኳስ ጋር ያለውን ቁርኝት ገና በአፍላ እድሜው ጀምሯል። በተለይ ደግሞ መኖሪያ ቤቱ አካባቢ የሚገኘው ሜዳ ላይ ጊዜውን ሲያሳልፍ የሚያያቸውን ታላላቆቹን የአካባቢው ተጫዋቾች በማድነቅ ወደ እግርኳሱ ተስቧል። እነ ሳልሃዲን ሰዒድን እያየ ያደገው የዛሬው ምርጥ ተጫዋች በጊዜው ማቲዎስ በፍቃዱ በሚያሠለጥነው የሰፈሩ ፕሮጀክ በመታቀፍ ወደ ታላቅነት የሚያደርገውን ጉዞ ጀምሯል። በዚህ የፕሮጀክት ቡድን ታቅፎ እያሰራ እያለም 2005 ላይ ሻሸመኔ ላይ በተደረገ ከ17 ዓመት በታች የክልል ሻምፒዮና ውድድር ላይ የሚሳተፍበትን እድል አግኝቶ ወደ ሻሸመኔ አቀና። በውድድሩ ላይም ድንቅ ብቃቱን በማሳየት በኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ የምልመላ ዕይታ ውስጥ በመግባት ይመልጥ ራሱን በሚያበቃበት አካዳሚ ገባ። ተጫዋቹ 2006 ላይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አካዳሚውን ከተቀላቀለ በኋላ ለሦስት ዓመታት በውስጡ ቆይቶ 2009 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የሚጫወትበትን አጋጣሚ በማግኘት ወደ አዳማ ከተማ አቀና። ለአዳማ ከተማም እስከ 2012 ለአራት ዓመታት ጥሩ ግልጋሎትን በመስጠት የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን እንዲያገለግል 2006 ላይ በአሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ (ኢንስትራክተር) ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጠው ተጫዋቹ በወቅቱ በነበረ የፓስፖርት ችግር በጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ሳይችል ቀርቷል። ከዛ ጊዜ ጀምሮም እስከ ዘንድሮ ድረስ ሀገሩን እንዲያገለግል ጥሪ ሳይቀርብለት ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲሱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተመርጦ በአሁኑ ሰዓት ብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውስጥ ይገኛል።

በፊት በፊት እርሱ እምብዛም ተጫዋቾች በማይፈሩበት ቤልሻል ጉምዝ ክልል ተወልዶ በአሁኑ ሰዓት የዘመናችን ከዋከብት ከሚባሉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ሱሌይማን ሀሚድ አጫጭር ጥያቄዎችን አቅርበንለት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

እኔ ታዳጊ እያለሁ በትልቅ ደረጃ ሲጫወቱ የነበሩት እነ ሳልሃዲን ሰዒድን እያደነቁ ነበር ያደኩት። አንድ ሰፈርም ስለነበርን እመለከታቸው ነበር። በተለይ ለእረፍት ወደ ሃገራቸው ሲመለሱም በቅርበት እከታተላቸው ነበር። በኢትዮጵያ እግርኳስም ትልቅ ነገር የሰራ ስለሆነ አርዓያዬ ሳልሃዲን ሰዒድ ነው።

ስምህ የተለየ ነገር እንዳለው አውቃለሁ። ስለ ስምህ የሆነ ነገር በለን?

በነገራችን ላይ በርካታ ሰዎች ስሜን ሱሌይማን ሰሚድ እያሉ ነው የሚጠሩኝ። ነገር ግን የእኔ ትክክለኛው መጠርያዬ ሱሌይማን ሐሚድ ሱሌይማን ነው ፤ አባቴ ነብሱን ይማረውና በጣም ይወደኝ ስለነበር በአያቴ ስም እንደጠራ በመፈለጉ ሱሌይማን ሐሚድ ሱሌይማን እንድባል አደረገ።

አሁን ለብሔራዊ ቡድን ከመጠራትህ በፊት እና ዓምና ሊጉ በኮቪድ ምክንያት ከተቆረጠ በኋላ ሰፊ ጊዜዎች ነበሩ። እነዚህን ጊዜያት በምንድን ነው ያሳለፍከው?

ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት ነበሩ። በተለይ ስፖርተኛ ያለመደው አኗኗርን ነበር ሲከተል የነበረው። ምንም ይሁን ግን እኔ የክልል ልጅ እንደመሆኔ እረፍቱን ተጠቅሜ ወደ ሀገሬ ተጉዤ ነበር። እዛም በውድድር ምክንያት በደንብ ያላገኘሁዋቸውን ቤተሰቦቼን በሰፊው አግኝቻለው። በአጠቃላይ በነበረው ሰፊ ጊዜ ጥሩ ጊዜን ከቤተሰቤ ጋር አሳልፌያለው።

በግልህ ጥሩ ጊዜን ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?

የእኔ ምርጡ ዓመት በአንፃራዊነት 2010 ላይ የነበረኝ ብቃት እና አቋም ነው። ቡድኔ አዳማም በዓመቱ ምርጥ ጉዞ እያደረገ ነበር። እስከ መጨረሻዎቹ ጨዋታዎችም ለዋንጫ ስንፎካከር ነበር። እርግጥ በመሐል ብድናችን ላይ ችግሮች ነበሩ። በዛም ዋንጫውን ሳናገኝ ቀርተናል። ግን እኔ በግሌ ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ። በተጨማሪም ዓምና በኮቪድ-19 ምክንያት ሊጉ እስኪቋረጥ የነበረኝ ብቃት ጥሩ ነበር።

ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህ ምንድን ናቸው?

ጠንካራ ጎኔን ብዙም ባልናገር ደስ ይለኛል። ሌሎች ሰዎች ቢመሰክሩ አሪፍ ነው። ግን ማንኛውንም ሰው አከብራለሁ። በዋናነት ከሰው ጋር ቶሎ የመግባባት ደካማ ጎን አለብኝ። ይህ ዋነኛ ደካማ ጎኔ ነው።

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን በምን ሙያ እናገኝህ ነበር?

አባቴ ነጋዴ ነበር። ይህንን ተከትሎ ወደ ንግዱ ዓለም የምገባ ይመስለኛል። በተለይ ከእርሱ ጋር ጊዜ አሳልፍ ስለነበር የተዋጣለት ነጋዴ እሆን ነበር።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለው የምትለው ተጫዋች አለ?

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን የሚገኘው የመሐል ተከላካይ አስቻለው ታመነ ነው። ብዙ ተጫዋቾችም ከእርሱ ጋር መጣመር ይፈልጋሉ። እኔም ከእርሱ ጋር መጫወት በጣም እፈልግ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከአስቻለው ጋር አሁን በብሔራዊ ቡድን ተገናኝተን ተጫወትን።

በተቃራኒው ስትገጥመው የሚከብድህ አጥቂ ወይም ተጫዋች አለ?

እስካሁን የገጠመኝ የለም።

በአሁኑ ሰዓት እየተጫወቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች የአንተ ምርጥ ተጫዋች ማነው?

በአሁኑ ሰአት አስቻለው ታመነ በጣም ድንቅ ብቃት ላይ ነው ፤ ስለዚህ ያለጥርጥር እሱ ነው የምመርጠው።

በአሁኑ ሰዓት እያሰለጠኑ ከሚገኙ አሰልጣኞችስ?

በታዳጊነት አሶሳ እያለሁ ያሰለጠነኝ ማቲዎስ በፍቃዱ እንዲሁም በአዳማ ከተማ ያሰለጠኑኝ አሸናፊ በቀለ ፣ አስቻለው ሃይለሚካኤል ፣ ተገኔ ነጋሽ ፣ ደጉ ዱባሞ የተሻለ ተጫዋች እንድሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። በአጠቃላይ ግን በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት አሰልጣኞች ከሆነ ጥያቄው አሸናፊ በቀለ እና ውበቱ አባተ እመርጣለው።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አጫውተኝ?

በተሰረዘው የውድድር አመት አዳማ እያለሁ ቡድናችን ውጤት ባጣበንበት ወቅት በሜዳችን ከኢትዮጵያ ቡናን አስተናግደን 3-0 ባሸነፍንበት ጨዋታ ላይ ግብ አስቆጥሬ ቡናን ያሸነፍንበት ጨዋታ መቼም የምረሳው አይደለም።

በእግርኳስ የተከፋበትስ አጋጣሚ አለ?

ጅማ አባጅፋር ዋንጫ ባነሳበት የ2010 የውድድር ዘመን ሊጉ አምስት ጨዋታዎች እስኪቀሩት ድረስ ሊጉን እየመራን ነበር ፤ በጥቃቅን ስህተቶች የሊጉን ዋንጫ ያጣንበት ያ የውድድር ዘመን በጣም የሚቆጨኝ አጋጣሚ ነበር።

በፊት የመስመር ተከላካይ አልነበርክም። በምን አጋጣሚ ነው በዚህ ቦታ መጫወት የጀመርከው?

የሚገርምህ ከፕሮጀክት ጀምሮ እስከ አካዳሚ ድረስ ስጫወት በአጥቂ ቦታ ላይ ነበር ስጫወት የነበረው። አዳማም ስፈርም በአጥቂነት ነበር። ግን በጊዜው አዳማ ቤት ታፈሰን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አጥቂዎች ነበሩ። በአንድ አጋጣሚ በሜዳችም ስንጫወት የመስመር ተከላካያችን በቀይ ካርድ ከሜዳ ይወጣብናል። ያንን ጨዋታ በሌላ የመስመር ተከላካይ አገባደን ወደ ዲቻ ተጉዘን ልንጫወት ስንል ግን ይህ ተከላካያችን ጉዳት አስተናገደ። ከዛም አሠልጣኝ ተገኔ ነጋሽ በድፍረት ትችላለህ ብሎኝ ቦታውን እንድሸፍን አደረገኝ። እኔም ቦታውን በአግባቡ በመሸፈን አሠልጣኞቼን አስደነቁ። በቀይ የወጣውም ሆነ የተጎዳው ተጫዋች ሲመለሱም እኔ በቦታው ምርጥ ስለነበርኩ እንድቀጥል ተደረገ። አንዳንዴም የመሐል ተከላካዮች ሲጎዱ ወደ መሐል እየገባው እጫወታለሁ። ግን በመስመር ተከላካይነት ቦታ መጫወት የጀመርኩት በዚህ አጋጣሚ ነው። አሁን ላይም በዚህ ቦታ ተመችቶኝ ነው እየተጫወትኩ ያለሁት።

ከእግርኳስ ከተገለለ በኋላ በምን ሙያ ለመዝለቅ ታስባለህ?

ገና እግርኳስን በከፍተኛ ደረጃ መጫወት ከጀመርኩ ጥቂት አመት እንደማስቆጠሬ ወደፊት የሚፈጠረውን አሁን ላይ ሆኜ መገመት ባልችልም እንደ አባቴ ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል።

ቅጥል ስም አለህ?

አብዛኛው ሰው ሱሌ ነው የሚለኝ ከዛ ውጭ አዳማ ቤት ሁለት ሱሌይማኖች ስለነበረን ሁለታችንን ለመለየት እኔን ትንሹ ሲሌይማ እየተባልኩ እጠራ ነበር።

ከኳስ ውጭ ምን ተሰጥኦ አለህ?

ከእግርኳስ ውጭ ብዙም ህይወት የለኝም ፤ እምነቴ ላይ ግን በጣም ትኩረት አደርጋለሁ።

ስለ ቤተሰብ ህይወትህ አውጋን እስኪ?

ፈጣሪ ይመስገን ትዳር በቅርቡ ይዣለሁ ፤ ከውዷ ባለቤቴ ጋር በአሶሳ እየኖርን እንገኛለን።

ከባለቤቱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዴት ተዋወክ?

የሚገርምህ ነገር የአንድ ሰፈር ልጆች ነን ፤ ቤታቸው የእህቷ ሰርግ ነበር ፤ እኔም ለእረፍት አሶሳ ባቀናሁበት ወቅት እነሱ ቤት የተዘጋጀውን ሰርግ ለመታደም በሄድኩበት ወቅት ነበር ከእርሱዋ ጋር የተዋወቅነው። ፈጣሪ ይመስገን አሁን የራሳችንን ሰርግ ሰርገን ለዚህ በቅተናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top