ወልዋሎ ጋናዊውን ለማስፈረም ሲስማማ ከተከላካዩ ጋር ተለያይቷል

ወልዋሎ ጋናዊውን ለማስፈረም ሲስማማ ከተከላካዩ ጋር ተለያይቷል

በውድድሩ ዓመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ ከተከላካዩ ጋር በስምምነት ተለያይተው ጋናዊውን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል።

ቀደም ብለው ሁለት ዩጋንዳውያንን ጨምሮ አራት ዝውውሮች ያገባደዱት ወልዋሎዎች አሁን ደግሞ  የመስመር ተጫዋች ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል። ክለቡን ለመቀላቀል ከስምምነት የደረሰው ተጫዋች ደግሞ ጋናዊውን መናፍ ዑመር ነው። ከዚህ ቀድም በጋናዎቹ ክለቦች ንሶአትርማን ፣ ሪል ታማሊ እና ኸርትስ ኦፍ ኦክ መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች በግራ መስመር አጥቂነት እና በአማካይነት መጫወት የሚችል ሲሆን በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ኸሳሙኤል ዮሐንስ ፣ ሀብታሙ ንጉሤ ፣ ፉዓድ አዚዝ ፣ ሙሳ ራማታህ እና ናይጄርያዊው ግብ ጠባቂ ኦሎሩንሌኬ ኦጆ ቀጥሎ ቡድኑን ለመቀላቀል የተስማማ ስድስተኛ ተጫዋች ለመሆን ከጫፍ ደርሷል።

ከወልዋሎ ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቢጫዎቹን ተቀላቅሎ ላለፉት ወራት ቡድኑን በማገልገል የቆየው ታዬ ጋሻው  ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።
ከአዳማ ከተማ ከተገኘ በኋላ በከፍተኛ ሊጉ ነገሌ አርሲ ቆይታ አድርጎ በድጋሚ ወደ አሳዳጊው አዳማ ከተማ ተመልሶ ለክለቡ ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ
በክረምቱ ወደ ወልዋሎ በማምራት በቢጫው መለያ አስር ጨዋታዎች አከናውኖ 896′ ደቂቃዎች ሜዳ ላይ የቆየው ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር በተደረገ ስምምነት ቀሪ ውል እየቀረው በጋራ ስምምነት ተለያይቷል።