ሁለት ተከታታይ ሽንፈት የገጠማቸው ቡድኖች በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ድል ለማግኘት የሚፋለሙበት ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነው
ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው በአራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን በማሳካት የመጀመርያውን ዙር ያጠናቀቁት ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በሃያ አምስት ነጥቦች የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት ኤሌክትሪኮች ደረጃቸውን ማሻሻል ይችሉባቸው የነበሩባቸውን የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዘው ካልተመለሱም ደረጃቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ዕድል ስላለ ጨዋታውን በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው የሚያከናውኑት ይሆናል። በነገው ዕለትም በሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ካስቆጠረ በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የፊት መስመር ወደ ቀደመው ውጤታማነቱ መመለስ ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይኖርበታል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍልም ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንጻር ነገ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም በመጨረሻው ጨዋታ የታዩት ግለ ሰባዊ ስህተቶችን ፈትቶ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በአስራ አምስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ከወራጅ ቀጠናው መውጣት የሚያስችላቸው ነጥብ ፍለጋ ኤሌክትሪክን ይገጥማሉ።
አንድ ነጥብ ብቻ ካሳኩባቸው ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ወልዋሎን አሸንፈው መጠነኛ እፎይታ ማግኘት ችለው የነበሩት ስሑል ሽረዎች ዳግም ወደ ተከታታይ የሽንፈት ጉዞ ተመልሰዋል። በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች ተተብትቦ ጨዋታዎቹን በማካሄድ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከወዲሁ በወራጅ ቀጠናው ካሉት ክለቦች ያለው የነጥብ ልዩነቱን አስፍቶ አጣብቂኝ ውስጥ ላለመግባት ወደ አሸናፊነት መመለስ ይኖርበታል። ይህ እንዲሆን ደግሞ በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ረገድ ያሉትን ክፍተቶች ማስተካከል የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የነገው ጨዋታ ዋነኛው ስራ መሆን ይገባዋል። በሊጉ ከወልዋሎ ቀጥሎ ጥቂት ግቦች ማስቆጠር የቻለው ቡድኑ በነገው ዕለትም የማጥቃት ክፍሉ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ኤልያስ አሕመድ ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ ማጣቱም ለአሰልጣኝ ጌታቸው ራስ ምታት ነው።
በኢትዮ ኤሌትሪክ በኩል ለወራት ከሜዳ ከራቁት በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና አብዱልአዚዝ አማን በቀር የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ተሟልተው የሚቀርቡ ይሆናል። በስሑል ሽረ በኩል ኤልያስ አሕመድ እና አማኑኤል ስንቀይ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ቡድኖቹ በመጀመርያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ ባዶ ለባዶ መጠናቀቁ ይታወሳል።