ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች |  ሀድያ ሆሳዕና ከ ባህርዳር ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች |  ሀድያ ሆሳዕና ከ ባህርዳር ከተማ

ነብሮቹን ከጣና ሞገዶቹ የሚያፋልመው መርሐ-ግብር የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው።


በሰላሣ ነጥቦች 4ኛ ደረጃ የተቀመጠው ባህርዳር ከተማ ደረጃውን ለማሻሻል በሁለት ነጥቦች ከሚልቀው ሀድያ ሆሳዕና ጋር ነገ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናል።

ለሽግግሮች እና ለመስመር አጨዋወቶች ቅድሚያ የሚሰጠው ባህርዳር ከተማ በቅርብ ሳምንታት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ አወንታዊ ለውጦች አምጥቷል ፤ ነገ ግን ጠንካራ የመከላከል ውቅር ባለው እና እምብዛም ክፍተት የማይሰጥ ተጋጣሚው የኋላ ክፍል ላይ ክፍተቶትችን ለማግኘት መፈተኑ የሚቀር አይመስልም።  የቡድኑ የፊት መስመር ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም ተጋጣሚው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ያስተናገደ እና ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ያለው ቡድን እንደመሆኑ የሚጠብቀው ፈተና ቀላል አይደለም።

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ደረጃቸው ለማሻሻል በሚያደርጉት ወሳኝ መርሐ-ግብር ምናልባትም የጨዋታው ውጤታቸው መወሰን በሚችለው የማጥቃት ጥንካሬ ልዩ ትኩረት አድርገው ይገባሉ ተብሎም ይገመታል።

በሰላሣ ሁለት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ኢትዮጵያ ቡና ከተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ደረጃቸው የሚያሻሽሉበት ዕድል አግኝተዋል።

ስድስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት አካባቢ የነበረው ሀድያ ሆሳዕና በቀጣዮቹ  ጨዋታዎችን ውስን መገራገጭ ቢገጥመውም አሁንም ከመሪዎቹ ጎራ አልራቀም።

ከመሪው በስድስት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ነብሮቹ መሪውን በቅርበት ለመከታተል እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ እና ወደ ድል መንገድ መመለስ ግድ ይላቸዋል። ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደው ክለቡ እምብዛም ግብ የማይቆጠርበት ጠጣር ቡድን ቢሆንም የማጥቃት አማራጮቹ ተገማች መሆን በቀላሉ ግቦችን እንዳያገኝ ያደረገው ይመስላል። በተደራጀ የመከላከል ውቅር የቀረቡት ቡድኖች  በገጠሙባቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች  በቂ የግብ ዕድሎች ያልፈጠሩት ነብሮቹ ነገም ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ ያለውና እምብዛም ክፍተት የማይሰጥ ቡድን እንደመግጠማቸው የባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድክመቶታቸው ማረም ይኖርባቸዋል። የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ቡድን በተጠቀሱት ሁለት ጨዋታዎች ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ከተጋጣሚው የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረጉ ባይካድም ተጋጣሚው ባህርዳር ከተማ በሊጉ ጥቂት ግቦች ካስተናገዱ ሦስት ክለቦች አንዱ እንደመሆኑ በብዙ ረገድ በተሻሻለ የማጥቃት ጥንካሬ ወደ ጨዋታው መቅረብ ግድ ይለዋል።

የነገው ጨዋታ ጥንቃቄን ምርጫቸው ያደረጉ እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም ጥረት የሚያደርጉ ቡድኖች የሚያገናኝ እንደመሆኑ የነጥብ መቀራረቡ ከሚፈጥረው ፍልምያ በተጨማሪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውም ተጠባቂ ያደርገዋል። 

በሀድያ ሆሳዕና በኩል መለሰ ሚሻሞ ፣ በረከት ወንድሙ እና ጫላ ተሺታ አሁንም በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ቃልአብ ውሸት ከቅጣት ይመለሳል። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ለወሳኙ ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። በጣና ሞገዶቹ በኩል ፍሬዘር ካሳ ቅጣቱን ባለመጨረሱ በነገው ጨዋታ ላይም አይኖርም፤ የተቀሩት የጣና ሞገድ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በተመሳሳይ አራት አራት ጊዜ ስያሸንፉ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱ የጣና ሞገዶቹ ሰባት ነብሮቹ ደግሞ  አምስት ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)