ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ስሑል ሽረን ያገናኘው የምሽቱ መርሐግብር በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኢትዮጵያ ቡና 1-ዐ በሆነ ውጤት በተሸነፉበት ጨዋታ ይዘው ከገቡት አሰላለፍ ሚኪያስ ካሳሁን ፣ ዲያንክ ከድር ፣ ሄኖክ ገብረሕይወት እና ኢዮብ ገ/ማርያምን አስወጥተው በምትካቸው ጌታሁን ባፋ ፣ አብዱላሂ አሊዩ ፣ አበባየሁ ዮሐንስ እና አቤል ሀብታሙን ሲያስገቡ በተቃራኒው ስሑል ሽረዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-0 በተሸነፉት ጨዋታ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ምሽት 12:00 ሲል በአ.ሳ.ቴ.ዩ ስታድየም የ 1-0 ሽንፈትን አስተናግደው በመጡት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተደረገው ጨዋታ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ምንም አይነት ሙከራ ሳያስመለክተን የቆየ የመጀመሪያ አጋማሽ ነበር። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ኳስን መስርተው ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በብዛት በመገኘት ለማጥቃት ጥረቶችን ሲያደርጉ በተቃራኒው መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ስሑል ሽረዎች በተከላካዮች በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች አልፎ አልፎ ለማጥቃት ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክቷል።
ምንም አይነት ሙከራዎችን ሳያስመለክተን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን የዘለቀው የምሽቱ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ሰዓት ሊጠናቀቅ 3 ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ያገኙትን የማዕዘን ምት ያሬድ የማነ ቀጥታ ከማዕዘን መትቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ባስመለከተን ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ጎል ሲደርሱ ተመልክተናል። ይሁን እና ሁለቱም ቡድኖች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ነበር። ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ጫና ፈጥረው የአቻነቱን ግብ ለማግኘት ሲታትሩ የነበሩት ስሑል ሽረዎች የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች የሰሩትን ግድግዳ መናድ ተስኗቸው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።