በ22ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት መርሐ ግብሮች መካከል ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ የነገው ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።
በሀያ አምስት ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀው ደረጃቸውን ለማሻሻል አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።
ሲዳማ ቡናዎች ባለፉት ሦስት መርሐ-ግብሮች ተከታታይ የአቻ ውጤቶች አስመዝግበዋል፤ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት አላማ ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባው አዳማ ከተማ በሚገጥሙበት ጨዋታም የሁለተኛውን ዙር አይን ገላጭ ድል ለማግኘት ዘርፈ ብዙ መሻሻሎች ማድረግ ይኖርባቸዋል። ቡድኑ እርግጥ ከባድ ተፋላሚ በገጠመበት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ለክፉ የማይሰጥ እንቅስቃሴ አድርጎ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ በአወንታነቱ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ግን አሁንም ወደ ውጤታማነት መድረስ አልቻለም። አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ የማጥቃት ክፍሉ ለማስተካከል በቀጣይ በፈጣን ሽግግሮች ለመጫወት እና ተጋጣሚ በሚተወው ክፍት ቦታ ላይ ያነጣጠረ የማጥቃት አቀራረብ ይዘው እንደሚቀርቡ ፍንጭ መስጠታቸው ተከትሎ በቡድኑ አጨዋወት ውስን ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ቡድኑ በነገው ዕለት በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስተናገደው አዳማ እንደመግጠሙ የሚጠብቀው ፈተና ከባለፉት ጨዋታዎች አንፃር አናሳ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ቢሆንም ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱ ግን የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያለበት ድክመት መቅረፍ ግድ ይለዋል።
በአስራ ዘጠኝ ነጥቦች 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አዳማ ከተማዎች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዘው መውጣት የሚችሉ ከሆነ ብያንስ የአንድ ደረጃ መሻሻል ያገኛሉ።
ከስድስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ካገኙበት የተከታታይ ሳምንታት ደካማ ውጤት በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በአርባምንጭ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በቶሎ አገግመው ደረጃቸው ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ። የላላው መከላከል አደረጃጀት የአዳማ ከተማ ዋነኛ ድክመት ነው፤ በሊጉ ሀያ ስምንት ግቦች በማስተናገድ ደካማ የመከላከል ቁጥር ያስመዘገበው ቡድኑ በነገው ጨምሮ በቀጣይ መርሐ-ግብሮች ወደ ውጤት ጎዳና ለመምጣትም የተጠቀሰው ድክመት መቅረፍ ግድ ይለዋል። ለተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት አቅቶት የነበረው የቡድኑ የፊት መስመር በቅርብ ሳምንታት ያሳየው መሻሻል በቡድኑ ከሚነሱ አወንታዊ ነገሮች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ለ450′ ደቂቃዎች ግብ ሳያስቆጥር ከዘለቀ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ያስቆጠረው ጠንካራ ጎንም ነገ መቀጠል የሚገባው ጥንካሬ ነው።
በሲዳማ ቡና በኩል ያሬድ ባዬ እና ደስታ ዮሐንስ አሁንም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን የመስፍን ታፈሰ የመሰለፍ ነገርም አጠራጣሪ ነው። አንተነህ ተስፋዬ እና ፍራኦል መንግስቱ ግን ከጉዳታቸው አገግመው ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ፤ ሌሎች የቡድኑ አባላትም ለጨዋታው ዝግጁ። መሆናቸውን አውቀናል። በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በጉዳት ሬድዋን ሸሪፍ ደግሞ በቅጣት የማይኖሩ ሲሆን የስንታየሁ መንግሥቱ እና የፍቅሩ ዓለማየሁ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በአንጻሩ ረዘም ላሉ ሳምንታት በጉዳት ያልነበረው ቢኒያም ዐይተን ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተረጋግጧል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በተገናኙባቸው 27 ጊዜያት ሲዳማ ቡና 9 አዳማ ከተማ ደግሞ 7 ጊዜ ድል ሲቀናቸው 11 ጨዋታዎች በአቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታተቻው ሲዳማዎች 23 አዳማዎችም በተመሳሳይ 23 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።