እጅግ ብርቱ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድኖች 2-1 በሆነ ውጤት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ መሪነታቸውን አጠናክረዋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው የ21ኛ ሳምንት መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማን 1-0 ያሸነፉት ኢትዮጵያ መድኖች ጨዋታውን ከጀመሩበት ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩላቸው ስሑል ሽረን 1-0 ባሸነፉበት ጨዋታ ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ተስፋዬ ታምራትን በዘላለም አበበ በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ሲል በ አ.ሳ.ቴ.ዩ ስታዲየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጥሩ የሚባል ፉክክርን ያስመለከተን ነበር። ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ በጥሩ መነቃቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ጫና በማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች የመጀመሪያ ግባቸውን ለማግኘት 9 ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁባቸው።የንግድ ባንኩ ተከላካይ ፈቱዲን ጀማል ለማቀበል ሲሞክር የሠራውን ስህተት ተከትሎ ኳሷን ያገኘው አለን ካይዋ ወደ ግብነት በመቀየር ኢትዮጵያ መድንን ገና በጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ መሪ ማድረግ ችሏል።
ኢትዮጵያ መድኖች የጎል ብልጫቸውን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ጥንቃቄን ምርጫቸው በማድረግ ጨዋታቸውን ቀጥለዋል። በፈጣን ሽግግር ወደ ተቃራኒ ግብ መድረስ የቻሉት ንግድ ባንኮች 18 ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ ከሳጥኑ ቀኝ መስመር ላይ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ይዞበታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ደጋግመው የመድኖችን የግብ ክልል ሲጎበኙ የነበሩት ንግድ ባንኮች ድካማቸው ፍሬ አፍርቶ 36ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም በግራ መስመር ኳስ ይዞ በመግባት ያቀበለውን ኳስ ኪቲካ ጅማ በድንቅ የመጀመሪያ ንክኪ የመድንን ተከላካይ በማለፍ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ድጋሚ ወደ መሪነታቸው ለመመለስ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች 49ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር መሐመድ አበራ ያሻማውን እና በንግድ ባንክ ተከላካይ ተጨርፎ ያገኘውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር በድጋሚ ኢትዮጵያ መድኖችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችም ከግቡ መቆጠር በኋላ ቅያሪዎችን በማድረግ ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህም ተቀይረው በገቡት ቢኒያም ካሳሁን እና ናትናኤል ዳንኤል አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በድጋሚ 77ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል በዛብህ ካቲሴ ከርቀት የመታው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ለንግድ ባንክ እጅግ አስቆጪ ሙከራ ነበር። 78ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል ከመድኖች ተጫዋች በመንጠቅ ከርቀት የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወጥቶበታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ውጥረት እና ግለት በነበረው ጨዋታ ጥፋቶች በዝተው የታዩበት ሲሆን ንግድ ባንኮች የመድንን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።