ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቻል ከ ፋሲል ከነማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቻል ከ ፋሲል ከነማ

መቻል እና ፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ በነገው ዕለት ከሚከናወኑ መርሐ-ግብሮች መካከል ተጠባቂው ነው።

ከድል ጋር ከተራራቁ ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት መቻሎች በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

መቻል በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገበው ውጤት በደረጃ ሰንጠረዡ እንዲንሸራተት ሆኗል፤ ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ከሊጉ ጠንካራ እና ውጤታማ የፊት መስመር ጥምረቶች አንዱ የነበረው የማጥቃት ጥንካሬውን ማጣቱ ነው። ባለፉት አራት መርሐ-ግብሮች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ቢያገግምም በሁለተኛው ዙር ሁለት መርሐ ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ነጥብ በላይ ማስመዝገብ አለመቻሉ ከፉክክሩ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እንዲቀር አድርጎታል። ሀያ ዘጠኝ ነጥቦች የሰበሰበው መቻል አሁንም ቢሆን ከፉክክሩ አልራቀም፤ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻለ በ2ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡ ክለቦች ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ ይላል። ይህ እንዲሆን ግን ለ360′ ደቂቃዎች ከግብ ጋር  የተኳረፈው የማጥቃት ክፍል ወደ ግብ ማስቆጠሩ መመለስ ይኖርበታል።

በሀያ አራት ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች መልስ ነገ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉ አንድ ደረጃ አሻሽለው ወደ ዕረፍት የማምራት ዕድል አላቸው።

ከተከታታይ ሁለት ድል በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ዐፄዎቹ ከስጋት ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ማሸነፍን እያሰላሰሉ የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ። ባለፉት አምስት የጨዋታ ሳምንታት ሦስቱም የውጤት ዓይነቶች ያስመዘገበው ቡድኑ እንደአብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች የወጥነት ችግር ይስተዋልበታል። ተከታታይ ድል፣ ተከታታይ ሽንፈት እና በአቻ ውጤት የታጀቡ ሳምንታት ያሳለፈው ፋሲል ከነማ በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ አመርቂ ብቃት አላሳየም። 
ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ የጠሩ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገረበት የአርባምንጩ ጨዋታ እንዲሁም ባህርዳር ከተማን በገጠመበት ተጠባቂው ደርቢ ላይ በቂ የግብ አጋጣሚዎች ባለመፍጠሩ በተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻለም፤ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደው መቻል በሚገጥምበት የነገው ጨዋታም የፈጠራ ችግሩ መቅረፍ ቀዳሚ ስራው መሆን ይኖርበታል።

የአሰልጣኝ ውበቱ አባተው ቡድን በቅርብ ሳምንታት ስላሳየው አወንታዊ ጎን እናንሳ ከተባለ ጨዋታን በመቆጣጠር ረገድ የነበረው ብቃት ነው፤  በነገው ጨዋታም የኳስ ቁጥጥር ላይ የበላይነቱን ሊይዙ እንደሚችሉ ቢገመቱም የተደራጀ የማጥቃት ኃይል አለመኖሩ ጨዋታውን ሊያከብድባቸው እንደሚችል ይገመታል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ስድስት ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻል አራት ጨዋታዎች አሸንፏል። ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው። ፋሲል 17 ሲያስቆጥር መቻል 10 ግቦች  አስቆጥሯል።