ሪፖርት| ምዓም አናብስት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል

ሪፖርት| ምዓም አናብስት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቀዋል

የቦና ዓሊ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ መቐለ 70 እንደርታን አሸናፊ አድርጋለች።

አርባምንጭ ከተማዎች አዳማ ላይ ድል ከተቀዳጀው ቋሚ ቡድን አህብዋ ብርያን እና በፍቃዱ መኮንንን በታምራት እያሱ እና ቻርለስ ሪባኑ ተክተው ሲገቡ ምዓም አናብስት ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ ኬኔዲ ገብረፃዲቅ፣ ቤንጃሚን ኮቴ እና መድሐኔ ብርሃኔን በሰለሞን ሐብቴ፣ ኪሩቤል ኃይሉ እና ቦና ዐሊ ተክተው ገብተዋል።

በሁሉም መመዘኛዎች ደካማ እንቅስቃሴ የታየበት የጨዋታው የመጀመርያ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር ብልጫው የወሰዱበት ቢሆንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግቶ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ግን አዞዎቹ ናቸው። ቡታቃ ሸመና በጨዋታው የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከቆመ ኳስ ተሻምታ በግንባሩ በመግጨት ያደረጋት ሙከራ እና ይሁን እንደሻው ከቆመ ኳስ አሻምቷት ታምራት እያሱ በግምባሩ ወደ ሳጥኑ አሻግሯት አሕመድ ሑሴን በማይታመን መልኩ ከግቡ አፋፍ ሆኖ ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስ በአዞዎቹ በኩል የተሞከሩ ናቸው። በአጋማሹ የጠራ የግብ ዕድል ያልፈጠሩት መቐለዎች ያሬድ ብርሃኑ ካደረጋት ዒላማዋን ያልጠበቀች ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ የተደረገበት ሁለተኛ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድሎች በመፍጠርም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የተሻሻሉበት ነበር። በአዞዎቹ በኩል ቡታቃ ሸመና ከርቀት አክርሮ መቷት ሶፎንያስ ሰይፈ ያዳናት እንዲሁም በተመሳሳይ አሕመድ ሑሴን እና ቻርለስ ሪባኑ ከርቀት አክርረው በመምታት ያደረጓቸው እና በግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ የከሸፉ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

ብሩክ ሙሉጌታ ከያሬድ ከበደ የተሻገረለትን ኳስ በመምታት ባደረጋት እና ለጥቂው ወደ ውጭ በወጣችው ሙከራ መሪ ለመሆን ተቃርበው የነበሩት መቐለዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ሲቀሩት በቦና ዓሊ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ሀፍቱ ከሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሯት በግቡ አፋፍ የነበረው ቦና ዓሊ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም የማታ ማታ መቐለን ባለ ድል ያደረገች ግብ ሆናለች።

ጨዋታው በመቐለ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ነጥቡን አስራ አምስት ማድረስ ሲችል አዞዎቹ ከተከታታይ ድሎች በኋላ ሽንፈት መቅመሳቸውን ተከትሎ በሊጉ አናት ካሉ ክለቦች ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠቡበት ዕድል አባክነዋል።