በእግድ ላይ የሚገኘው የክለቦች እና የተጫዋቾች የቅጣት ውሳኔ ምን ሂደት ላይ ይገኛል?

በእግድ ላይ የሚገኘው የክለቦች እና የተጫዋቾች የቅጣት ውሳኔ ምን ሂደት ላይ ይገኛል?

የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደርን በተመለከተ በቅርቡ የተወሰነው ውሳኔ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማጣራት አድርገናል።

ከወራቶች በፊት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አባላቱ ከሆኑት ክለቦች ጋር በመምከር የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ በማውጣት ካሳለፍነው የዝውውር መስኮት ጀምሮ ከዝውውር እና ከደሞዝ ጋር ተያይዞ ያለውን የክለቦች የፋይናንስ እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት እና የህግ ባለሙያዎች የተወጣጣ ኮሚቴ በማቋቋም እጅግ ውስብስብ የሆነውን የዝውውር ሂደት ሲመረምር የቆየው ኮሚቴው የካቲት 17 የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር  1/2016 በአንቀጽ 7 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት  በ4 ክለቦች እና በ15  ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ ክለቦቹ  የቅድመ ክፍያ(በሦስተኛ ወገን) በመክፈላቸው እና ተጫዋቾቹ በመቀበላቸው በአንቀጽ 5 የተከለከሉ ተግባራት ስር የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ጥሰዋል በሚል የቅጣት ውሳኔዎችን ማስተላለፉ አይዘነጋም።

ቅጣት የተላለፈባቸው ክለቦች እና ተጫዋቾች ወዲያው ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ያሉ ሲሆን ኮሚቴውም “ጉዳዩን እስክመረምር ፍትህ የሚጓደል ይሆናል” በሚል ውሳኔውን አግዷል። ታዲያ ጉዳዩ ያለበትን ሂደት ለማጣራት የሞከረችው ሶከር ኢትዮጵያ የሂደቱን አሁናዊ መረጃዎች ከውስጥ ምንጮቿ እንደሚከተለው አግኝታለች።

በዚህም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሊጉ አክሲዮን ማኅበር በክለቦቹ እና ተጫዋቾቹ ላይ ቅጣት እንዲተላለፍ ያስቻለውን ሰነድ እና ማስረጃ እንዲያቀርብ በጠየቀው መሰረት የአክሲዮን ማኅበሩ የህግ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ሰነድ አደራጅተው ከትናንት በስትያ (ማክሰኞ) ለይግባኝ ሰሚ እንዳስገቡ ለማወቅ ችለናል። እርግጥ በቅድሚያ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ውሳኔውን የካቲት 21 ከወሰነ በኋላ በ5 ቀናት ሰነዶቹ እንዲቀርቡ ቢያስቀምጥም ተጨማሪ ዝርዝር ጥያቄዎች ቀርበው እስከ ትናንት ድረስ ሰነዱ እንዲቀርብ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ስለነበር አክሲዮን ማኅበሩ ቀነ ገደቡን ተንተርሶ ሰነዱን አስገብቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይ ኃላፊዎች በፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ ማድረጋቸውን የሰማን ሲሆን በስብሰባው ከተነሱ የጋራ የስራ ሂደቶች መካከል በፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ውሳኔዎች ዙሪያ እንደሆነ ሰምተናል። እርግጥ ከስብሰባው የተነሳ ውሳኔ ባይኖርም ጉዳዩ የህግ ስርዓቱን ተከትሎ እንዲቋጭ አቅጣጫ መቀመጡን አውቀናል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከትናንት በስትያ የደረሰውን ሰፊ ሰነድ ተንተርሶ ከጉዳዩ አንገብጋቢነት እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡን ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ በቅርቡ ውሳኔውን እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ይሆናል።