👉 “ስጋቴ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ ለምን በዚህ ሰዓት ማድረግ እንዳስፈለገ አልገባኝም። በዚህ ሰዓት ቡድናችን ልምምዱን እያደረገ ይገኛል ለእኔ ይሄ አሳማኝ አይደለም።”
👉 “ወደዚህ ለጉብኝት አልመጣንም ፤ አሸንፈን እንደምናልፍ እርግጠኞች ነን።”
👉 “አብዛኛው ካሜሩናዊ ገዘፍ ያለ አካላዊ ቁመና አለን ከዛም መነሻነት ሊሆን ይችላል…..”
ለ2026 ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የተገናኙት ካሜሩን እና ኢትዮጵያ ካሜሮን ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ አስተናጋጇ ሀገር 5ለ2 ማሸነፏ ይታወሳል። ሆኖም ነገ በአ.አ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከሚደረገው የመልስ ጨዋታ በፊት የሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች ዛሬ ከሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን በቅድሚያም የአሰልጣኝ ራውዳ ዓሊን ሀሳብ አጋርተናችሁ ነበር አሁን ደግሞ የካሜሩን ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ የሆኑትን ኢድዊን ቴተህ ሀሳብ እናጋራችሁ
“ከፈጣሪ ጋር የተሻለ ነገር ለማድረግ ተዘጋጅተን ጨዋታውን እየተጠባበቅን እንገኛለን ፤ ስጋቴ ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ለምን በዚህ ሰዓት ማድረግ እንዳስፈለገ አልገባኝም። በዚህ ሰዓት ቡድናችን ልምምዱን እያደረገ ይገኛል ለእኔ ይሄ አሳማኝ አይደለም። በተመሳሳይ ሰዓት መግለጫ መስጠት እና ልምምድ ማሰራት አንችልም። ወደዚህ ስንመጣ ቀድመን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደምንሰጥ ጠብቄ ነበር ፤ ነገርግን ይህ አልሆነም በመሆኑም ይሄ መሆኑ ስጋት ይፈጥርብኛል።”
“ወደዚህ ለጉብኝት አልመጣንም ፤ አሸንፈን እንደምናልፍ እርግጠኞች ነን። ቡድናችን ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሰጠ ነው በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ጥሩ ተጫዋቾች አሉን በተለይ በመከላከሉ ረገድ በጣም ጠንካራ አደረጃጀት አለን ከዚህ ባልተናነሰ ማጥቃታችን የተሻለ የሚባል ነው።”
“ከእድሜ ተገቢነት ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች መልሴ የእኛ ልጆች ከአካዳሚዎች የተሰባሰቡ ናቸው ፤ አብዛኞቹ ልጆች በካምሩን ሁለተኛ ዲቪዝዩን ከሚገኙ ክለቦች የተመረጡ ናቸው። በተፈጥሮ አብዛኛው ካሜሩናዊ ገዘፍ ያለ አካላዊ ቁመና አለን ከዛም መነሻነት ሊሆን ይችላል። እኛ ከዚህ ቀደም ግብፅን ጥለን ስናልፍ ከእኛ ልጆች አንፃር ግዙፎች ነበሩ ነገር ግን እኛ ቅሬታ አላቀረብንም እኛ ላይም የሚቀርበው ጥያቄ ለምን እንደሆነ አይገባኝም።”