“የአማካይ ክፍላችን እንቅስቃሴ ደካማ ስለነበር ተሸንፈናል።” አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ
“የኢትዮጵያ ቡድን ኳስን ይዞ ለመጫወት የሚሞክር መሆኑ በመሃል ሜዳ ላይ እንድንቸገር አድርጎናል።” ረዳት አሰልጣኝ ኤድዊን ቴተህ
በ2026 የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታ ካሜሮን ኢትዮጵያን 1ለ0 በድምሩ 6ለ2 ካሸነፈችበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ !
አሰልጣኝ ራውዳ ዓሊ – ኢትዮጵያ
“ጨዋታው ለኛ ትንሽ ከበድ ያለ ነበር፤ እንደነበረው እንቅስቃሴ ክፍተቶች ማግኘት ከብዶን ነበር። በይበልጥ አጥቅተን ለመጫወት ነበር ያሰብነው፤ ቦታ ማግኘት አልቻልንም የአማካይ ክፍላችን እንቅስቃሴ ደካማ ስለነበር ተሸንፈን ለመውጣት ችለናል። የእነሱ እንቅስቃሴ ቦታዎች መሸፈን ነው፤ ቅድም እንዳልኩት የኛ አማካዮች ስናጠቃ ቦታ እየፈለጉ አልነበረም ሰው በሰው ‘Marking’ አልነበረም ብዬ ነው የማስበው።
የሚኒስትሪ ተፈታኟ ሊዲያ ኢያሱ ስላደረገችው ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ…
“ታዳጊ ስለነበረች ከዕረፍት በኋላ ቀይሪያት ለውጥ ስላየሁ ከዛ በተጨማሪ ልምምድ ላይ በማየው ለውጦች የተሻለች ስለነበረች ነው የመጀመርያ ተሰላፊ ያደረግኳት፤ ነገ ከነገ ወዲያ ለሀገር ትጠቅማለች በሚለው እዚህ ትልቅ ጨዋታ ላይ ቅድሚያ እንድሰጣት ሆኗል። ያደረገችው እንቅስቃሴ ደካማ ነው ብዬ አላስብም ግን ከነሱ ተክለ ቁመና አንፃር የኛ አጥቂዎች በተክለ ቁመና ስለሚበለጡ እሷ ቢያንስ እንኳን እንድትሸፍነው ነበር የተወሰነ ነገር ሰርታልናለች ብዬ ነው የማስበው። ታዳጊ ስለሆነች ነገ የተሻለ ነገር ትሰራለች ብዬ አስባለሁ።”
ረዳት አሰልጣኝ ኤድዊን ቴተህ – ካሜሮን
“በጣም አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር ፤ በትላንቱ የቅድመ ጨዋታ መግለጫዬ እንደተናገርኩት ጨዋታ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገምተን ነበር።የኢትዮጵያ ቡድን ኳስን ይዞ ለመጫወት የሚሞክር መሆኑ በመሀል ሜዳ ላይ እንድንቸገር አድርጎናል ከዛ ባለፈ በአየር ንብረቱ የተነሳ ልጆቻችን በአተነፋፈስ ረገድ ተቸግረው ነበር።”