የቀድሞው የግብ ዘብ የግብ ጠባቂዎች ማሰልጠኛ ሊከፍት ነው

የቀድሞው የግብ ዘብ የግብ ጠባቂዎች ማሰልጠኛ ሊከፍት ነው

ካሜሩናዊው የቀድሞው የግብ ዘብ ቤሊንጋ ኤኖህ በኢትዮጵያ የግብ ጠባቂዎች ማሰልጠኛ ሊከፍት ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ አስራ ሦስት ዓመታት አልፈውታል ፤ ለሐረር ቢራ ፣ ለአዲስ አበባ ውሃ ሥራዎች፣ ለመቐለ ሰባ እንድርታ፣ ለወልድያ ከተማ ፣ ለወልቂጤ ከተማ ፣ ለሀዋሳ ከተማ እና በመጨረሻም ለሀላባ ከተማ አገልግሎት ሰጥቷል። በሊጉም ወልድያ ከተማ በነበረበት ወቅት ለክለቡ 45 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በተከታታይ ከማድረጉ ባሻገር ሚያዚያ 24 2009 ድሬዳዋ ላይ ወልዲያ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ቤሊንጋ ከረጅም ርቀት በ14ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠሩ በብዙዎች የስፖርት ቤተሰቦች ይታወቃል።

በቋሚነት ኑሮውን በአዲስ አበባ ያደረገው የግብ ዘቡ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ከቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አልፍያ ጃርሶ ጋር በመሆን ቤሊንጋ ኢኖህ እግርኳስ አካዳሚ በመክፈት በሴት እና በወንድ ከ84 በላይ ታዳጊዎችን በመያዝ እያሰለጠነ ይገኛል።

አሁን ደግሞ ግብ ጠባቂዎች ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ወደ ስራ እንደሚገባ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፆል።

ይህንን ስልጠና ለመስጠት ያነሳሳውን ምክንያት ሲገልፅ “ በሌሎች ሀገራት የሚሰጠውን የግብ ጠባቂዎች ስልጠና በኢትዮጵያ አለመኖሩ እና ያለውን የግብ ጠባቂዎችን ክፍተት ለመቅረፍ ያለውን ልምድ ተጠቀወሞ ለክለብም ሆነ ለብሔራዊ ቡድን የሚበቁ ግብ ጠባቂዎችን ለማፍራት” ያለመ እንደሆነ ተናግሯል።