የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር የሊጉን የበላይ አካል ማብራሪያ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር የሊጉን የበላይ አካል ማብራሪያ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በሊጉ የክለቦች ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ክፍያ ጋር በተያያዘ የሦስት ጋዜጠኞች ስም አለ ማለቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ማብራሪያ ጠይቋል።

ከወራቶች በፊት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አባላቱ ከሆኑት ክለቦች ጋር በመምከር የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ በማውጣት ካሳለፍነው የዝውውር መስኮት ጀምሮ ከዝውውር እና ከደሞዝ ጋር ተያይዞ ያለውን የክለቦች የፋይናንስ እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት እና የህግ ባለሙያዎች የተወጣጣ ኮሚቴ በማቋቋም እጅግ ውስብስብ የሆነውን የዝውውር ሂደት ሲመረምር የቆየው ኮሚቴው የካቲት 17 የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር  1/2016 በአንቀጽ 7 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት  በ4 ክለቦች እና በ15  ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ ክለቦቹ  የቅድመ ክፍያ(በሦስተኛ ወገን) በመክፈላቸው እና ተጫዋቾቹ በመቀበላቸው በአንቀጽ 5 የተከለከሉ ተግባራት ስር የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ጥሰዋል በሚል የቅጣት ውሳኔዎችን ማስተላለፉ አይዘነጋም።

ይህንን የቅጣት ውሳኔ በተመለከተ አክሲዮን ማኅበሩ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገለፃ ሲያደርግ በህገወጥ ድርጊቱ ሦስት ጋዜጠኞች መኖራቸውን ጠቅሶ በቅርቡም የጋዜጠኞቹ ስም ይፋ እንደሚሆን አመላክቶ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር በጉዳዩ ዙርያ ማብራሪያ እንዲሰጠው በይፋዊ መንገድ ጥያቄ አቅርቧል።

ማኅበሩ ባወጣው ደብዳቤ “ጉዳዩ የስፖርት ጋዜጠኞችን ስም እና ዝና የሚያጎድፍ፣ ስነልቦናዊ ጫናም የፈጠረ ነው።” ካለ በኋላ አክሲዮን ማኅበሩ አለኝ የሚለውን መረጃ ማውጣት ካልሆነ ደግሞ ዝም ማለት ሲገባው “ሀሜት” በሚመስል መልኩ መረጃውን ማውጣቱ ተገቢ አይደለም ብሏል። በመጨረሻም አክሲዮን ማኅበሩ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል።