በመጨረሻው ጨዋታ ከገጠማቸው የአንድ ለባዶ ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚገቡት መቻል እና መቐለ 70 እንደርታ የሚያደርጉት ጨዋታ 12:00 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
ድል ካደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ያለፋቸው መቻሎች
በሀያ ዘጠኝ ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሁለት መልክ ያለው፤ በተከታታይ ድሎች እና በተከታታይ ሽንፈቶች የታጀበ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው መቻል በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ሊጉን እስከመምራት ቢደርስም ሳይጠበቅ ደረጃው ተንሸራቶ ወደ ስጋት ቀጠናው ይበልጥ ተጠግቷል። ካለው ጥሩ ስብስብ አንፃር ከሚጠበቅበት ውጤት በታች እያስመዘገበ የሚገኘው ቡድኑ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ ያለበትን ድክመት መቅረፍ ይኖርበታል፤ በተለይም በፊት መስመሩ ላይ የሚስተዋለው የግብ ማስቆጠር ድክመት አንገብጋቢ መፍትሔ የሚሻው ጉዳይ ነው። ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻሉት መቻሎች ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ እና ደረጃቸው ለማሻሻል
ከምንም በላይ ጎል ፊት ያላቸው ድክመት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
መቻል በቀጣይ መርሐ-ግብሮች በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ ካልቀረበ ከፊቱ ያለው አደጋ አስጊ ነው፤ በ14ኛ ደረጃ ላይ ካለው የነገው ተጋጣሚው መቐለ 70 እንደርታ ያለው የነጥብ ልዩነት 4 ብቻ መሆኑም በውጤት ረገድ ቡድኑ ያለበትን አሁናዊ ሁኔታ ማሳያ ነው።
በሀያ አምስት ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከአንድ ጨዋታ በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ እና ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመላቀቅ በነገው ዕለት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።
ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ካስተናገዱ በኋላ አርባምንጭ ከተማን በማሸነፍ መጠነኛ እፎይታን አግኝተው የነበሩት ምዓም አናብስት በመጨረሻው ጨዋታ በወላይታ ድቻ የገጠማቸው ሽንፈት በደረጃ ሰንጠረዡ በአንድ ዝቅ እንዲሉ አድርጓቸዋል። በመጀመርያዎቹ ስድስት ሳምንታት የአዳማ ከተማ ቆይታቸው ሽንፈት ሳይቀምሱ ከዘለቁ በኋላ በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ ሽንፈት ያስተናገዱት መቐለዎች ከ 12 እስከ 16 ሳምንት ድረስ የነበረባቸው የመከላከል ጥንካሬ ለማስቀጠል መቸገራቸው ቡድኑን ለተደጋጋሚ ሽንፈት ዳርጎታል። በቅርብ ጨዋታዎች ዳግም ወደ አራት የተከላካዮች አደራደር የተመለሱት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በቀጣይ የመከላከል አደረጃጀቱን ጥንካሬ መመለስ እና የወጥነት ችግር የሚስተዋልበት የፊት መስመራቸው ላይ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በመቻል በኩል አስቻለው ታመነ እና ግሩም ሀጎስ ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ ሲያገግሙ ባሳለፍነው ጨዋታ በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የነበረው ዳዊት ማሞ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተጠቁሟል። ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳት ያስተናገደው በረከት ደስታ ግን ባለማገገሙ ከጨዋታው ውጪ እንደሆነ ተመላክቷል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ጉዳት ላይ የነበረው ያሬድ ብርሃኑ ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ የመድረሱ ነገር አልታወቀም፤ ሔኖክ አንጃው እና ተመስገን በጅሮንድ ግን ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆነዋል።
መቐለዎች ወደ ሊጉ በመጡበት የ2010 የውድድር ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች መቐለ 70 እንደርታ 3 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን መቻል አንዱን አሸንፏል፤ አንዱን ደሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው። በግንኙነቱ መቐለ 9 ሲያስቆጥር ጦሩ 5 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።