ሪፖርት | የረፋዱ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

ሪፖርት | የረፋዱ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የጦና ንቦቹ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ጎል ተለያይተው ከሊጉ መሪ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 6 ማጥበብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በረፋዱ ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በ23ኛ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 3ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ስንታየሁ መንግሥቱ ፣ ኤልያስ ለገሰ ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና አሸናፊ ኤልያስን አስወጥተው ነቢል ኑሪ ፣ አድናን ረሻድ ፣ መላኩ ኤልያስ እና ፉዓድ ኢብራሂምን ሲያስገቡ የጦና ንቦቹ በአንጻሩ መቐለ 70 እንደርታን 1ለ0 ያሸነፉበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።

ረፋድ 3፡30 ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የጦና ንቦቹ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ ጎል በተደጋጋሚ የመድረስ እና የአዳማ ከተማ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ሲሞክሩ የተስተዋለበት ነበር።

የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራም 7ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማዎች አማካኝነት ሲደረግ አድናን ረሻድ ከቀኙ የሳጥን ጠርዝ አካባቢ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶበታል።

በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታውን ያስቀጠሉት የጦና ንቦቹ 14ኛ ደቂቃ ላይ ጎል ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ቴዎድሮስ ታፈሰ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሲያሻማ ኳሱን ያገኘው ውብሸት ክፍሌ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈራ እና በግቡ የቀኝ ቋሚ ተመልሶበታል።

ወላይታ ድቻዎች ተጭነው እየተጫወቱ ቢቀጥሉም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ለማድረግ ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን ቴዎድሮስ ታፈሰ አሻምቶት ካርሎስ ዳምጠው የገጨው እና ፍጹም ግርማ አሻግሮት ያሬድ ዳርዛ የገጨውን ኳስ በተመሳሳይ ናትናኤል ተፈራ በቀላሉ ይዟቸዋል። ይህም የአጋማሹ የመጨረሻ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የመጀመሪያውን ሙከራ ማድረግ የቻሉት አዳማዎች 54ኛ ደቂቃ ላይ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል አግኝተው ነበር። ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ዐይተን ያስቆጥረዋል ተብሎ ሲጠበቅ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በተመሳሳይ ሂደት በቀጠለው ጨዋታ የጦና ንቦቹ በጥሩ ቅብብል 66ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ሳጥን ውስጥ አብነት ደምሴ ባመቻቸለት ኳስ ያሬድ ዳርዛ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈራ በግሩም ብቃት አክሽፎበታል።

ቀስ በቀስ ግለቱ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ በአዳማ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ኤልያስ ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ሞክሮት ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በቀላሉ የያዘበት ኳስ ተጠቃሽ ነው። የአዳማ ከተማ የመከላከል አደረጃጀትም ጥንካሬውን እያሳየ መዝለቅ ችሏል።

84ኛው ደቂቃ ላይ በወላይታ ድቻ በኩል ዘላለም አባተ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ላይ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣበት 87ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን እና ግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈራ መቆጣጠር ያልቻለውን ኳስ ያገኘው ብሥራት በቀለ ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይህም በጦና ንቦቹ በኩል እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም 0-0 ተጠናቋል።