ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ያመራው ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ አዲስ መረጃ ተሰምቷል

ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ያመራው ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ አዲስ መረጃ ተሰምቷል

የኢትዮጵያ ለፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የካቲት 15 ቀን 2017 ያስተላለፈው ውሳኔ በፍርድ ቤት ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ እንዲታገድ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

የሊጉ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1/2016 በአንቀጽ 7 በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በአራት ክለቦች እና በ15  ተጫዋቾች ላይ ባደረገው ምርመራ ክለቦቹ የቅድመ ክፍያ (በሦስተኛ ወገን) መክፈላቸውን እና ተጫዋቾቹ መቀበላቸውን አረጋግጫለው በማለት የቅጣት ውሳኔዎችን በክለቦቹ እና በተጫዋቾቹ ላይ ማስተላለፉ ይታወቃል። ቅጣት የተጣለባቸው አካላት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ቢሉም ይግባኛቸው ውድቅ የተደረገ ሲሆን ከቀናት በፊትም መቻል እና ሲዳማ እንዲሁም ተጫዋቾቻቸው ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ አክሲዮን ማኅበሩን መክሰሳቸውን ዘግበን ነበር።

የህግ ባለሙያ በመቅጠር ጉዳያቸውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ይዘው በመሄድ ክስ የመሰረቱት መቻል እንዲሁም ተጫዋቾቹ ምንይሉ ወንድሙ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ፣ ደሳለኝ ከተማው፣ ነስረዲን ኃይሉ፣ በረከት ደስታ፣ አማኑኤል ዩሐንስ፣ ዳዊት ማሞ፣ መስፍን ታፈሰ፣ ደስታ ደሙ፣ ፍራኦል መንግስቱ፣ ሀብታሙ ታደሰ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ያሬድ ባየ የተላለፈባቸው ውሳኔ በፍርድ ቤት ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ እንዲታገድ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን ሶከር ኢትዮጵያ የከሳቾችን ጉዳይ ከያዙት ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው ማረጋገጥ ችላለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የእግርኳስ ክለቦች ንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ በንግድ ህጉ መሰረት አዋጅ ተከትሎ የግል ትርፍ መከፋፈል የሆነበትን የተቋቋመበትን ዓላማ ስቶ የሰጠው ውሳኔ ተገቢነት የሌለው መሆኑን እና የወጣው ደንብም ከህግ አግባብ ውጪ በማለት ደንቡ እንዲሻሻል የተጠየቀ ሲሆን የመቻል እና የሲዳማ ቡና ተጫዋቾችም የአክሲዮን አባልነት እና የድርሻ የገቢ ክፍፍል ስምምነት የሌላቸው መሆኑን ጠቅሶ የሊጉ የበላይ አካል በሌለው ስልጣን እና ተግባር በከሳሾች ላይ ተገቢ ውሳኔ መወሰኑን እንዲሻር ቢጠየቅም ተከሳሽ አስተያየት ሳይሰጥበት ዕግድ ሊሰጥ ስለማይገባ በትናትናው ዕለት ከሳሾች ያቀረቡት የዕግድ አቤቱታ ለተከሳሾች ደርሶ አስተያየቱን በፅሁፍ ለ20/08/2017 እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።