ሪፖርት | ስሑል ሽረ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠረበት ጎል ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

ሪፖርት | ስሑል ሽረ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠረበት ጎል ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

በ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ስሑል ሽረ 1-1 ተለያይተዋል።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከኢትዮጵያ መድን ነጥብ ከተጋራ ቡድን ሳሙኤል ዮሐንስ እና ፉሃድ አዚዝ ለውጥ ሲያደርግ ዳዊት ገብሩ እና ዳዋ ሆጤሳ በምትኩ አስገብተዋል። በሲዳማ ቡና የተረቱት ስሑል ሽረ ባለፈው ከተጠቀሙበት ቋሚያቸው ውስጥ
ክፍሎም ገብረሕይወት እና ብርሃኑ አዳሙን በፋሲል አስማማው እና አብዲ ዋበላ ያደረጉት ሁለት ቅያሪያቸው ሆኗል።

የ25ኛ ሳምንት የመክፈቻ  መርሐ ግብር በፌደራል ዳኛ ባህሩ ተካ እየተመራ በጀመረው ጨዋታ የመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ወልዎሎዎች በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ከወሰዱት ብልጫ ውጭ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጠራ የጎል ሙከራዎችን በሁለቱም በኩል አልተመለከትንም። በ24ኛው ደቂቃም ስሑል ሽረ ከሳጥን ውጭ በቀኝ መስመር ያገኙትን ቅጣት ምት አሰጋኸኝ ያሻገረውን ነፃነት በግንባሩ ሲጨርፈው ጥዑመልሳን ኃይለሚካኤል አግኝቶ መረብ ላይ በማሳረፍ ስሑል ሽረዎችን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ሜዳውን ለጥጠው በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ቢጫ ለባሾቹ ሦስተኛው የሜዳው ክፍል ላይ ሲደርሱ በቀላሉ በሚቆራረጡ ኳሶች ምክንያት ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ይሁን እንጂ በሁለት አጋጣሚዎች አደጋ የፈጠሩ ሲሆን በተለይ ናትናኤል ዘለቀ 25ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ያገኘውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ስሑል ሽረዎች በጥንቃቄ እየተጫወቱ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ይቆዩ እንጂ ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ ወደ ፊት በመሄድ የፈጠሩት አደገኛ ሙከራ አልነበረም።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በሁለቱም በኩል ሁለት ፈጣን ቅያሪዎችን አድርገዋል። ጨዋታውም ክፍት የነበረ በመሆኑ በሁለቱም በኩል ለማጥቃት በሚደረጉ ምልልሶች በጎል ሙከራ አይታጀብ እንጂ ጨዋታው ከፍ ባለ ግለት እንዲቀጥል ሆኗል። 69ኛው ደቂቃም ስሑል ሽረዎች ከግራ መስመር አላዛር ሽመልስ በጥሩ መንገድ ያሻገረለትን ተቀይሮ የገባው ብርሀኑ አዳሙ ሳይጠቀምበት የቀረ ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ነው።

የጨዋታው የመጨረሻው አስር ደቂቃ ወልዋሎዎች አቻ መሆን የቻሉበትን ጎል በ81ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከሜዳው ግራ ክፍል የተሰጠውን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ዮሐንስ ያሻገረውን ተከላካዮ ቃሲም ረዛቅ በጥሩ አጨራረስ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ስሑል ሽረዎች ተመልሰው መምራት የሚችሉበትን ዕድል ብርሃኑ አዳሙ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ኦሎሩንለኬ በቀላሉ የያዘበት እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ ያለፈው እንዲሁም ብዙም ሳይቆይ በቅብብሎች ወልዋሎ ሜዳ የደረሱት ስሑል ሽረዎች ከግራ መስመር  የተሻገረለትን በተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ጃዕፈር ሙዳሲር አግኝቶ ወደ ጎል የመታው ለጥቂት የወጣው ለሱሑል ሽረ ሌላ የጎል አጋጣሚ ነበር። በጨዋታው መጠናቀቂያ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የሱሑል ሽረው አንበል ነፃነት ገብረመድህን ዳዋ ሆጤሳ ላይ ከእንቅስቃሴ ውጭ ጥፋት ሰርተሀል በሚል በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጎ ጨዋታው 1-1 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።