ሪፖርት | መቻል ተከታታይ ድል አሳክቷል

ሪፖርት | መቻል ተከታታይ ድል አሳክቷል

መቻሎች በሽመልስ በቀለ ብቸኛ ግብ አዞዎችን 1ለ0 ማሸነፍ ችለዋል።

በኢዮብ ሰንደቁ

በ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቻልን ከአርባምንጭ ከተማ ሲያገናኝ ባሳለፍነው ሳምንት መቻሎች መቐለ 70 እንደርታን ካሸነፉበት አሰላለፍ በኃይሉ ግርማን በኮሊን ኮፊ በመተካት ጨዋታዎቸውን ሲጀምሩ በተመሳሳይ አርባምንጭ ከተማዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ ብሩክ ባይሳ እና ፍቃዱ መኮንን በማስወጣት በምትካቸው አሸናፊ ፊዳ እና አንዱዓለም አስናቀን አስገብተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ፈዘዝ ያለ ጨዋታን ያስመለከተን አጋማሽ ሲሆን ጥፋቶች እና የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ጨዋታ ነበር። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ጨዋታ የነበረ ሲሆን በኳሱ ቁጥጥሩ ረገድ መቻሎች በመጠኑም ቢሆን የተሻሉ ነበሩ። ኳስን ከራሳቸው የሜዳ ክፍል መስርተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የሚደርሱት መቻሎች ኳሱን ወደ ግብ ሙከራ መቀየር ላይ ግን አዳጋች ሁኖባቸው ነበር።  በተቃራኒው መከላከሉ ላይ አተኩረው የሚጫወቱት አርባምጮች ከመከላከል የሚያገኙትን ኳስ በረጃጅም ኳስ እና በመልሶ ማጥቃት ግብን ለማግኘት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታ በዘለለ ይሄ ነው የሚባል ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ መቻሎች በጨዋታ የተሻሉ ነበሩ የማጥቃት መነሻቸውን በመስመር ከማድረግ በስተቀር ምንም የጨዋታ ለውጥ ሳያስመለክተን ጨዋታው ቀጥሏል። 70ኛው ደቂቃ ላይ ግን መቻሎች እጅግ ለግብ የቀረበ አስቆጪ ሙከራን ማድረግ ችለው ነበር። ከራሳቸው የግብ ክልል ከተከላካዮች መነሻውን ያደረገውን ኳስ ኮሊን ኮፊ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሽመልስ በቀለ ግብጠባቂውን በማለፍ ቢሞክርም በግቡን አግዳሚ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ይሄ የመጀመሪያ ሙከራቸው በር የከፈተላቸው መቻሎች ከሁለት ደቂቃ በኋላ በመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸው የመጀመሪያ ግባቸውን አሽቆጥረዋል። 72ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው በረከት ደስታ የሰጠውን ኳስ ሽመልስ በቀለ የአርባምንጭ ተከላካዮችን አታሎ በመግባት ጥሩ በሆነ አጨራረስ ግብ በማስቆጠር መቻልን መሪ ማድረግ ችሏል። አርባምንጭ ከተማዎች ከግቡ መቆጠር በኋላ አቻ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቶ በመቻል 1-0 መሪነት ጨዋታው ተጠናቋል።