ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

በሦስት ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖች በየፊናቸው የሁለት ደረጃዎች መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ድል ለማግኘት ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋሉ።

ከአስራ አንድ ጨዋታዎች በኋላ፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ አዳማን ሦስት ለአንድ ማሸነፍ ከቻሉ በኋላ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ነጥብ የተጋሩት ድሬዳዋ ከተማዎች መጠነኛ እፎይታ አግኝተዋል። ሆኖም አሁንም ከስጋት ቀጠናው  ባለመራቃቸው የነገውን ከባድ ጨዋታ በማሸነፍ ሁለት ደረጃዎችን የማሻሻል ዕድላቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል።

ከነገው ተጋጣሚያቸው በሦስት ነጥቦች ዝቅ ብለው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ብርቱካናማዎቹ ከአደጋው ለመራቅ ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። በአዳማ ድል ሳያደርግ ከተማውን ከተሰናበተ በኋላ በ23ኛው ሳምንት በቅርብ ተፎካካሪው ወሳኝ ድል የተጎናፀፈው ቡድኑ ከውጤቱም ባሻገር በቅርብ ሳምንታት ጥሩ ለውጦች አስመዝግቧል። በተለይም በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከዘለቀ በኋላ በመጨረሻዎች ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ክፍል በብዙ ረገድ ተሻሽሏል። ሆኖም ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደም ጨዋታዎች ለመቆጣጠር መቸገሩ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለን የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው። ከመጨረሻው ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት የድህረ ጨዋታ ቆይታ ቡድናቸው ካለበት የስጋት ቀጠና መነሻነት ተጫዋቾቹ በነፃነት ለመጫወት መቸገራቸው የጠቀሱት አሰልጣኙ በነገው ዕለትም ከተጋጣሚያቸው አንፃር ሲታይ ከፍ ባለ ጫና  ወደ ጨዋታው እንደመግባታቸው ቡድናቸው በአእምሮ ረገድ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

በሃያ ዘጠኝ ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የሁለተኛው ዙር ጉዟቸው ለማቃናት ከብርቱካናማዎቹ ጋር ይፋለማሉ።

ኤሌክትሪኮች በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን ማሳካት ቢችሉም በሁለተኛው ዙር በፉክክሩ የነበራቸው ፍጥነት ቀንሶ በተከታታይ ጨዋታዎች ለመሸነፍ ተገደዋል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት፣ አንድ ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ የተንሸራተተው ቡድኑ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርጎ ሁለት ደረጃዎችን ለማሻሻል በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የሚከወን ጨዋታ ነው። ባለፉት ጨዋታዎች የወትሮውን የመስመር ጥቃት አስፈሪነቱ ማስቀጠል ያልቻለው የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ላይ በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች መፍጠር ቢችልም የአፈፃፀም ችግር ዋነኛ ድክመቱ ነበር። ቡድኑ ምንም እንኳን በቀድሞ ልክ ባይሆንም ዕድሎች መፍጠር መጀመሩ በአወንታ የሚነሳለት ነጥብ ነው፤ ሆኖም ግብ አከባቢ ያለበት ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል።

ድሬዳዋ ከተማዎች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው መሐመድኑር ናስር ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ጉዳት ላይ የነበረው ያሬድ ታደስም አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጉዳት ላይ የከረመው አብዱላዚዝ አማን ለነገው ጨዋታ ሲደርስ በፍቃዱ አስረሳኸኝ ልምምድ ቢጀምርም ወደ ጨዋታ ለመግባት ግን ቀጣይ ሳምንቶችን የሚጠብቅ ይሆናል። የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች ተሟልተው  የሚቀርቡ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ17 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ6፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ4 አጋጣሚዎች ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። ኤሌክትሪክ 20 ድሬዳዋ ደግሞ 14 ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል።