በሦስት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች ከሽንፈት ለማገገም የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
አራት ነጥቦች ብቻ ከጣሉባቸው ሰባት ውጤታማ መርሐ-ግብሮች በኋላ በመጨረሻው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ገጥሟቸው ደረጃቸውን የማሻሻል ዕድል ያባከኑት ወላይታ ድቻዎች በፉክክሩ ለመዝለቅ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ይኖርባቸዋል።
የጦና ንቦቹ አራት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡ በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከአዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተው በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት አስተናግደዋል፤ ቡድኑ ነጥብ በጣለባቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የፊት መስመሩ ላይ መጠነኛ ችግር እንዳለም አስመልክቷል።
በ14ኛ ሳምንት በተደረገው እና ወልዋሎን ሁለት ለባዶ ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ በተደረጉ አስራ አንድ መርሐ-ግብሮች ላይ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት የፊት መስመሩ ላይ ውስን የአፈፃፀም ክፍተቶችን ሲያስመለክት ነበር፤ ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ግብ ማስቆጠር ያልቻለ ሲሆን
በተለይም በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ባስተናገደበት የመጨረሻው ጨዋታ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ስል ሙከራዎችን ማድረግ ተስኖት ነበር። ከዚህ መነሻነት ይህን የቅርብ ጊዜ ድክመቱን ካላረመ በነገው ጨዋታ ሊጎዳ ይችላል።
በሰላሣ አራት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የ2ኛውን ዙር የመጀመርያው ድል ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ነብሮቹ ከ7ኛ እስከ 15ኛ ሳምንት ድረስ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው 24 ነጥቦች 22 በማሳካት ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ ቢችሉም በመጨረሻዎቹ አስር ጨዋታዎች ግን በብዙ መለክያዎች ተዳክመዋል፤ በተጠቀሱት መርሐ-ግብሮቹም በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነበር ድል ማድረግ የቻሉት። ከመጀመርያው ዙር አጋማሽ በኋላ ያሳዩት ወጥነት ያለው ብቃት ማስቀጠል ያልቻሉት ነብሮቹ በፉክክሩ የነበራቸው ፍጥነት ቀንሶ የነበሩበት ደረጃ በማስረከብ በሰንጠረዡ አሽቆልቁለዋል፤ ለዚ እንደ ምክንያትነት የሚነሳው ደግሞ የማጥቃት ክፍሉ መዳከም ነው። ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥብ፤ አስራ አራቱን ጥለው አራቱን ብቻ ባሳኩባቸው ያለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠራቸውም ቡድኑ ከቀደመው ውጤታማ የአፈፃፀም ብቃቱ በእጅጉ እንደተዳከመ ማሳያ ነው።
በነገው ዕለትም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ በጠንካራ ወቅታዊ ብቃት የሚገኘው የጦና ንቦች የተከላካይ ክፍል እንደመግጠማቸው በማጥቃቱ በኩል ያሉባቸው ድክመቶች ማረም ይጠበቅባቸዋል።
ወላይታ ድቻ ወሳኙን ግብጠባቂ ቢንያም ገነቱን በአምስት ቢጫ በቅጣት ከመጣቱ ውጭ ሌላ የጉዳትም የቅጣት ዜና የለም። በነብሮቹ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት በረከት ወንድሙ፣ ጫላ ተሺታ ፣ መለሰ ሚሻሞ እና የሄኖክ አርፊጮ አሁንም ጉዳት ላይ መሆናቸው ሲሰማ በተጨማሪም ሰመረ ሀፍታይ በጉዳት ተቀላቅሎቸዋል። ከዚህ ውጭ ቃልአበ ውብሸት እና በረከት ወልደዮሐንስ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠማቸው ሲሆን ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ነገርም አጠራጣሪ ነው። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ11 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ወላይታ ድቻ አምስት ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ አራት ጨዋታዎች አሸንፈዋል፤ የተቀሩ ሁለት መርሐግብሮች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።