ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ወልዋሎ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ድል የተራቡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ከኢትዮጵያ መድን እና ስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ተጋርተው የወጡት ወልዋሎዎች በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው ከወዲሁ ላለማጨለም በነገው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ የማግኘት ግዴታ አለባቸው።

ወልዋሎ በ 11 ነጥብ በሊጉ ግርጌ ላይ መገኘቱ እንዲሁም ከወራጅ ቀጠናው ጋር ካሉት ሌሎች  ቡድኖች ጋር ያለው ልዩነት ሰፊ እንደመሆኑ በሊጉ ለመቆየት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል፤ በቀጣይ መርሐ-ግብሮችም ድል ማስመዝገብ ብቸኛው አማራጩ ነው። ከሁለተኛው ዙር መጀመር በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ በተለይም በጨዋታ በአማካይ አንድ ግብ ባስቆጠረባቸው ያለፉት ሦስት መርሐ-ግብሮች በማጥቃቱ በኩል ውስን መሻሻል ማሳየት ቢችልም ውጤት ማስጠበቅ እንዲሁም ግለ-ሰባዊ ስህተቶች መቀነስ ተስኖታል።

ቀጣይ መርሐ-ግብሮች ልክ እንደ ዋንጫ ጨዋታ እየተመለከተ በተለየ ትኩረት ማከናወን የሚጠበቅበት ቡድኑ ከላይ የተጠቀሱት ድክመቶች ከመቅረፍ ባለፈ ግቦች በማስቆጠር እንዲሁም በስነ-ልቦና ረገድ በብዙ መንገድ በመሻሻል በሊጉ ለመቆየት ያለው እንጥፍጣፊ ዕድል ለመጠቀም  ተዘጋጅቶ መቅረብ ይኖርበታል።

11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊጉ መሪዎች ጎራ ከነበረባቸው ጊዜያት ወርዶ በ31 ነጥቦች በሰንጠረዡ አካፋይ ላይ ተቀምጧል።

ወላይታ ድቻን ሁለት ለባዶ ከረቱ በኋላ ስምንት ጨዋታዎችን ያለድል የተጓዙት ፈረሰኞቹ በሁለተኛው ዙር በተከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ስምንት ነጥቦች ማሳካት የቻሉት ሁለቱን ብቻ ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በሊጉ እስከ 18ኛው ሳምንት ድረስ ተከታታይ ሽንፈት ሳይቀምስ ቢዘልቅም ከዛ በኋላ በተከናወኑ ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ ሽንፈት ማስተናገዱም ያለበትን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ፈረሰኞቹ በእርግጥ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር  ነገ ሙሉ ውጤት ማግኘት ከቻሉ  በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ የሚሉበት ዕድል ቢኖርም የራቃቸውን የድል መንፈስ መልሶ ማግኘት ግን በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ በመጀመርያው አጋማሽ የተወሰደባቸው ብልጫ በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ በውስን መልኩ ቀልብሰው የግብ ዕድሎች መፍጠራቸው እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ጉዳይ ቢሆንም በግብ ማስቆጠሩ እንዲሁም የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች በማቆም ረገድ የነበረባቸው ድክመት ግን መቀረፍ የሚገባው ነው።  በተለይም የቀድሞ ጥንካሬው መመለስ ያልቻለው እና በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የፊት መስመር የአፈፃፀም ድክመቱን ቶሎ መቅረፍ ግድ ይለዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከባለፈው የጨዋታ ሳምንት በተለየ የተሰማ አዲስ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለም፤  በመሆኑም ሻይዱ ሙስጠፋ፣ ተገኑ ተገሙ፣ ፍሪምፖንግ እና አብዱልሐፊዚ ቶፊቅ አሁንም ጉዳት ላይ ናቸው። ወልዋሎዎች ፉዐድ አዚዝ እና ሙሳ ራማታህ  ከቅጣት መልስ ስያገኙ በነገው ጨዋታም ከቅጣት እና ጉዳት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 4 ጊዜያት ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ሲያሸንፍ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ፈረሰኞቹ 4 ሲያስቆጥሩ ቢጫ ለባሾቹ 1 አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ እንዲሁም በ2011 ሁለተኛው ዙር ላይ ያልተካሄደው ጨዋታ አልተካተተም)