ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና

ሁለቱ ቡናዎች የድል መንገዳቸውን ለማስቀጠል በዕለተ ትንሣኤ የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሰላሣ ዘጠኝ ነጥቦች በመሰብሰብ ከመሪው መድን በዘጠኝ ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻው ሳምንት ያገኙትን ወሳኝ ድል በማስቀጠል መሪው እስኪጫወት ድረስ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ተዘጋጅተው ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይገመታል።

በድሎች ከታጀቡ ሰባት ሽንፈት አልባ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በባህር ዳር ከተማ ከገጠማቸው ሽንፈት አገግመው ፋሲል ከነማን በማሸነፍ ወደ 2ኛ ደረጃነት ከፍ ያሉት ቡናማዎቹ መሪው ላይ ጫና ለማሳደር በነገው ዕለት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ሁለተኛው ጥቂት ግብ ያስተናገደ፤ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ በሰባቱ መረቡን አስከብሮ ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የመከላከል መዋቅር ያለው ቡድን ነው። የአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ ልጆች በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ስራ በመከወን ላይ ቢገኙም በማጥቃቱ በኩል ያላቸው ጥንካሬ ግን እምብዛም ነው፤ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ በሆኑ ቀጣይ መርሐግብሮችም  በሰንጠረዡ አናት ላይ ይበልጥ ተፅዕኖ ለመፍጠር ማጥቃታቸው ተለዋዋጭ ማድረግ እንዲሁም የአፈፃፀም ብቃታቸው ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በሰላሣ ሁለት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ከረዥም ጊዜያት በኋላ ያሳኩት ተከታታይ ድል አስቀጥለው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በሊጉ በርከት ያሉ ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ካጠናቀቁ ክለቦች የሚጠቀሱት ሲዳማ ቡናዎች በቅርብ ሳምንታት ድል ማድረግ ከመጀመራቸው በተጨማሪ የቡድኑ እንቅስቃሴም መሻሻሎች አሳይቷል፤ ቡድኑ ሽንፈት ቢያስተናግድም በአመዛኙ ብልጫ ወስዶ በርከት ያሉ ዕድሎች በፈጠረበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ እንዲሁም ተከታታይ ድል ባስመዘገበባቸው መርሐግብሮች ያሳየው እንቅስቃሴም የዚህ ማሳያ ነው።  በአፈፃፀም በኩል አሁንም መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም ባለፉት ጨዋታዎች ተስፋ ሰጪ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ካለባቸው ስጋት ነፃ ለመሆን የሚያስችሏቸውን ነጥቦች ለማሳካት ለጠንካራው የኢትዮጵያ ቡና የኋላ ክፍል የሚመጥን አቀራረብ ማበጀት ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተጋጣሚያቸው ካለበት ጥሩ አቋም እና ከፍ ያለ የማሸነፍ ስነ ልቦና አንፃር ራሳቸውን በአዕምሮው ረገድ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተከላካዩ ወልደአማኑኤል ጌቱ ልምምድ ላይ ካጋጠመው ጉዳት ባለማገገሙ በነገው ጨዋታ ላይም አይኖርም። በሲዳማ ቡና በኩል በቅጣትም በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ የሆነ ተጫዋች የሌለ ሲሆን በባለፈው ጨዋታ  ውጭ የነበሩት ያሬድ ባየህ እና ይገዙ ቦጋለ ቡድኑን የተቀላቀሉ መሆኑን አውቀናል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በአጠቃላይ 29 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 10 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን በ10 ጨዋታ አቻ ተለያይተው 9 ጨዋታ ሲዳማ ቡና አሸንፏል። ኢትዮጵያ ቡና 37 ሲዳማ ቡና 30 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።