ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አርባምንጭ ከተማ ከ ስሑል ሽረ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | አርባምንጭ ከተማ ከ ስሑል ሽረ

አርባምንጭ ከተማ እና ስሑል ሽረ የሚያደርጉት ጨዋታ በበዓለ ትንሳሤው ዕለት የሚደረግ ሁለተኛው መርሐግብር ነው።

ሁለተኛውን ዙር በፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ባስመዘገቧቸው ተከታታይ ድሎች ጀምረው ከዛ በኋላ በተካሄዱ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች በሰላሣ አራት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

አዞዎቹ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካታቸውን ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ አሽቆልቁለዋል፤ ነጥብ በጣሉባቸው ጨዋታዎች የነበረው እንቅስቃሴም በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ነው። ቡድኑ እንደወትሮው ወደ ራሱ የግብ ክልል ቀርቦ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ባደረገባቸው መርሐግብሮች በመከላከሉ ረገድ የነበረበት ጥንካሬ በጥሩ ጎኑ የሚነሳለት ቢሆንም የግብ ዕድል በመፍጠርም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ የነበረበት ድክመት ግን በጉልህ ይነሳል። በተለይም በመቻል ሽንፈት ባስተናገደበት የመጨረሻው መርሐግብር የጠሩ ዕድሎች መፍጠር አልቻለም። አሰልጣኝ በረከት ደሙ ከዚህ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የነበረው ውጤታማው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥንካሬ ከመመለስ በተጨማሪ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከታየው ወጥነት የጎደለው አካሄድ መውጣት ይኖርባቸዋል። በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘትም የቡድኑ የአሸናፊነት መንፈስ ከመመለስ በዘለለ ቢያንስ የሁለት ደረጃዎች መሻሻል የሚያስገኝ እንደመሆኑም ፋይዳው ብዙ ነው።

የድል ብርሀንን ካዩ ስድስት ሳምንታት ያለፏቸው ስሑል ሽረዎች በወራጅ ቀጠናው ካሉ ክለቦች ያላቸው የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ከናፈቃቸው ድል ጋር መታረቅ ግድ ይላቸዋል። ስሑል ሽረዎች ባለፉት 13 የጨዋታ ሳምንታት ከአንድ ድል እና ሦስት አቻ ውጭ በተቀሩት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግደዋል፤ ቡድኑ በተጠቀሱት ሳምንታት ያስመዘገባቸው ውጤቶችም ለምን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ እንዳለ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ ያሳየው እንቅስቃሴ በቀጣይ የተሻለ ግምት እንዲሰጠው ያደረገ ቢሆንም ቀጥለው በተካሄዱ መርሐግብሮች ግን ለውጡን ማስቀጠል ሳይችል ቀርቷል። ስሑል ሽረዎች ምንም እንኳን የሚቆጠሩባቸውን ግቦች መቀነስ ቢችሉም በአንድ ጎል ልዩነት ለሽንፈት መዳረጋቸው አልቀረም፤ የመጨረሻዎቹ ሰባት ሽንፈቶችም በተመሳሳይ በአንድ ለባዶ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። በሊጉ የመቆየት ተስፋው ለማለምለም ወሳኝ ድል ማስመዝገብ የሚጠበቅበት የአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ቡድን በቀዳሚነት ዋነኛ ድክመቱ የሆነው የግብ ማስቆጠር ችግር መፍታት ግድ ይለዋል። ቡድኑ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር ከዘለቀ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ ኳስ እና መረብ ማገናኘት ቢችልም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ይኖርበታል።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል እንዳልካቸው መስፍን ከጉዳት ብሩክ ባይሳ ደግሞ ከቅጣት ቢመለሱም ተከላካዩ በርናንድ ኦቼንግ በጉዳት እንዲሁም አጥቂው አህመድ ሁሴን በቅጣት  ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። በስሑል ሽረ በኩልም ነፃነት ገብረመድኅን በቅጣት ክፍሎም ገብረህይወት ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሳተፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ አዞዎቹ በቡታቃ ሸመና ብቸኛ ግብ ማሸነፋቸው ይታወሳል።