በወራጅ ቀጠናው ፉክክር የሚገኘው አዳማ ከተማ እና የዋንጫ ፉክክሩን ለመቀላቀል እየታተረ የሚገኘው መቻል አስፈላጊ ድል ለማግኘት የሚፋለሙበት ጨዋታ ነገ ረፋድ ይካሄዳል።
ድል ካደረጉ አምስት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት አዳማ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ የሆነ ጨዋታ ያከናውናሉ።
በሁለተኛውን ዙር ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ቢጀምሩም ቀጥለው በተካሄዱ መርሐ-ግብሮች በጨዋታ ከአንድ ነጥብ በላይ ማሳካት ያልቻሉት አዳማ ከተማዎች በሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ላይ ባለው ፉክክር ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋሉ። በአንድ ደረጃ እና በሦስት ነጥቦች ከፍ ብሎ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻው መርሐ-ግብር ያሳካው ድልም የዚህን ጨዋታ ዋጋ ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል። ቡድኑ ድል ቢቀናውም የደረጃ መሻሻልን የሚያገኝበት ዕድል ባይኖርም ከተፎካካሪዎቹ ላለመራቅ ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘር አስፈላጊው ይሆናል።
በደካማ የውድድር ዓመት እዚህ የደረሱት አዳማ ከተማዎች በቅርብ ሳምንታት ጉልህ የሆነ የወጥነት ችግር ተስተውሎባቸዋል፤ በርግጥ ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች መላቀቁ አሁንም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚደረገው ፉክክር ተስፋ እንዲሰንቅ የሚያደርገው ቢሆንም አንዴ ሞቅ አንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚለው የመከላከል ጥምረቱ ሁኔታ ማረም ግድ ይለዋል። አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደው እና በውድድር ዓመቱ የቡድኑ ዋነኛ ድክመት ሆኖ የዘለቀው የመከላከል ችግር በቀዳሚነት መፍታት የሚጠበቅባቸው ሲሆን በግብ ማስቆጠሩ በኩል ያለባቸው ድክመትም ሌላው መሻሻል የሚገባው ጉዳይ ነው።
በሰላሣ አምስት ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች ከአስራ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የሚጠጉበት ዕድል አመቻችተዋል፤ በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻሉ ብያንስ ሁለት ደረጃዎች የሚያሻሽሉበት ዕድል ስላለም ጨዋታው በቀላሉ የሚመለከቱት አይደለም። በ2ኛ ደረጃ ከተቀመጠው ቡና በአራት ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከጨዋታው በሚገኙ ነጥቦች ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የመጠጋት ዓላማ ይኑረው እንጂ ሙሉ ለሙሉ በፉክክሩ ውስጥ ለመሳተፍ በዚህ ጨዋታ ድል ከማዝመዝገብ ባለፈ በወጥነት መዝለቅ ግድ ይለዋል።
በርግጥ ጦሩ ከተከታታይ ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ መጀመሩ እንዲሁም መሪው በመከተል በሚገኙ ቡድኖች ላይ በሚታየው የወጥነት ችግር አሁንም ፉክክሩን ለመቀላቀል ሰፊ ዕድል አለው፤ ይህ እንዲሆን ግን በቅርብ ሳምንታት የታየው የድል ረሀብ ማስቀጥል እንዲሁም ውስን መሻሻል ያሳየው የማጥቃት ክፍሉ ጥንካሬ ማዳበር ይኖርባቸዋል። በተለይም በስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ በማስቆጠር ደካማ ሳምንታት ካሳለፈ በኋላ በቅርብ ሳምንታት ውስን መሻሻል ያሳየው የማጥቃት አጨዋወት እንዲሁም ጨዋታን በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ እመርታ ያሳየው የአማካይ ክፍል ጥንካሬዎች ማስቀጠል የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የቤት ስራዎች ናቸው።
በመቻል በኩል ዮሴፍ ታረቀኝ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ ሲያመልጠው ሌሎቹ ተጫዋቾች ለፍልሚያው ዝግጁ እንደሆኑ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።በአዳማ ከተማ በኩል ደግሞ ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
መቻል እና አዳማ በሊጉ 34 ጨዋታዎች አከናውነዋል። በግንኙነቱም መቻል 11 ጊዜ ስያሸንፍ አዳማ ከተማ 10 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርጓል፤ የተቀሩት 13 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተገባደዱ ናቸው። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 57 ግቦች ውስጥ መቻል 29 አዳማ ደግሞ 28 ግቦችን አስመዝግበዋል።