የጣና ሞገዶቹ ከሽንፈት ለማገገም ምዓም አናብስት ደግሞ ድላቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ሦስተኛ መርሐ-ግብር ነው።
በሰላሣ ሰባት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች በመጨረሻው መርሐ-ግብር ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም ምዓም አናብስትን ይገጥማሉ።
ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ፤ በ2ኛው ዙር ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ደረጃቸውን ለማስረከብ የተገደዱት የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ ድል ከቀናቸው ወደ 2ኛ ደረጃነት ከፍ የሚሉበት ዕድል ስለሚያገኙ በመጨረሻው መርሐ-ግብር በሲዳማ ቡና ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም ወደ ድል መንገድ መመለስ ይኖርባቸዋል። በመጨረሻው ጨዋታ ሽንፈት ማስተናገድ ቢችሉም በተለይም ጫና በፈጠሩበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት የጣና ሞገዶቹ በአፈፃፀሙ በኩል የነበረባቸው ድክመት ከጨዋታው ነጥብ ይዘው እንዳይወጡ አድርጓቸዋል። የወጥነት ችግር ቢስተዋልበትም በአምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ማስቆጠር ችሎ የነበረው የማጥቃት ጥምረቱም የጨዋታ ውጤት ቀያሪ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ያሉበትም ክፍተቶች ማረም ይኖርበታል። ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ የመከላከል ውቅር ያለው በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የሚታትር ጠጣር ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በመከላከሉ ረገድ ይዘውት የዘለቁት ጥንካሬ ማስቀጠል ቢችሉም በማጥቃት ክፍሉ የሚታየው መዋዥቅ በቡድኑ የወጥነት ጉዞ ላይ እክል ሆኗል።
በውድድር ዓመቱ በመደዳ ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ቡድኑ በቀጣይ ላለበት የፉክክር ደረጃ የሚመጥን ተከታታይነት ያለው ብቃት ለማሳየት የመከላከል ጥንካሬው በማስቀጠል በተጋጣሚ ግብ አከባቢ ላለበት ችግር መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅበታል።
በሀያ ስምንት ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በመጨረሻው ሳምንት ሀድያ ሆሳዕና ላይ የተቀዳጁት ድል በመድገም ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ነብሮቹን በማሸነፍ በ2ኛው ዙር ሁለተኛ ድላቸውን ያሳኩት ምዓም አናብስት ከስድስት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኃላ በተከናወኑ መርሐ-ግብሮች በውጤት ረገድ ነገሮች በአወንታ አልሄደላቸውም። በ2ኛው ዙር ከተከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ ሽንፈት ማስተናገዳቸውም ከስጋት ቀጠናው ፈቀቅ እንዳይሉ አድርጓቸው ነበር፤ በ25ኛ ሳምንት የተመዘገበው ድል ግን ለቡድኑ መጠነኛ እፎይታ የሰጠ ሆኖ አልፏል። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ በተገኘው ድል ከወራጅ ቀጠናው በመጠኑ መራቅ ቢችልም ከስጋት ቀጠናው ስጋት ሙሉ ለሙሉ ለመራቅ ግን ተከታታይ ድሎች ማስመዝገብ ይኖርበታል።
ነብሮቹን ባሸነፈበት መርሐ-ግብር ከወትሮ የተሻለ የቡድን እንቅስቃሴ እና የማጥቃት ደመ ነፍስ የነበረው ቡድኑ በጨዋታው ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ተስፋ ሰጪ ነገር አሳይቷል፤ በጨዋታውም ኳሱን በተሻለ በመቆጣጠር ከወገብ በታች በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ የነበሩትን የነብሮቹ ተጫዋቾች ለማስከፈት ታትረዋል። በነገው ዕለት የሚገጥሙት ቡድን ግን በሊጉ ሁለተኛው ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደ እና በ2ኛው ዙር በተካሄዱ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት በቀላሉ ግቡን የሚያጋልጥ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ስለሆነ የሚገኙ አጋጣሚዎችን በስልነት መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ሽንፈት ባስተናገደባቸው ጨዋታዎች በቀላሉ ሲጋለጥ የነበረው የተከላካይ ክፍሉ እንዲሁም የተስተዋሉት ተደጋጋሚ የግል ስህተቶች በዘላቂነት መፍታት ከቡድኑ ይጠበቃል።
በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድን አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ግን አማካዩ ኬኔዲ ገብረፃዲቅ በሕመም ሔኖክ አንጃው ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከተሰረዙት ሁለት የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታዎች ውጭ በፕሪምየር ሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጨዋታዎች ሲሸናነፉ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ግቦችንም አስቆጥረዋል።