ድሬዳዋ ከተማ በአሥራት ቱንጆ ብቸኛ ጎል ፋሲል ከነማን 1ለ0 አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን ልዩነት ወደ አምስት ነጥቦች አስፍቷል።
ዐፄዎቹ በቡናማዎቹ ከተረቱበት ስብስባቸው ምኞት ደበበ፣ ጃቢር ሙሉ እና ቢንያም ጌታቸውን በማሳረፍ ዳንኤል ፍፁም፣ አቤል እንዳለ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በመተካት ለጨዋታው ሲቀርቡ ። በአንፃሩ ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የነበራቸውን ጨዋታ በከባድ ዝናብ ምክንያት ጨዋታቸውን ያላደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች በ24ኛ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስባቸው ሙኸዲን ሙሳ እና አቡበከር ሻሚልን አስቀምጠው ሄኖክ ሀሰን እና ሱራፌል ጌታቸውን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደጻድቅ ባስጀመሩት ጨዋታ መመጣጠን የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጅማሮ በ6ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጭ ከቅጣት ምት በሞከረው ጠንካራ ምት ጥሩ የጎል ዕድል ዐፄዎቹ ፈፅመው ነበር። ጨዋታው ተመጣጣኝ ከሆነ ፉክክር ወጥቶ ምንም የጠራ ሙከራ ወደ ማይደረግበት ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ አምርቷል። በ21ኛው ደቂቃም በረጅሙ የተላከውን ኳስ ሐቢብ ከማል በግብ ጠባቂው ፋሲል እና በተከላካይ ኢዮብ መሐል ሾልኮ ያሸነፈውን ኳስ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ኢዮብ ወደ ውጭ ያወጣበት በብርትካናማዎቹ በኩል የተፈጠረ አጋጣሚ ነበር።
ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ አንድ ደቂቃ እየቀረ በማጥቂያው ቀኝ ክፍ ቢንያም ላንቃሞ ከግብ ጠባቂው አላዛር ጋር ታግሎ የተቀበለውን ኳስ ሲያሻመው አማኑኤል ለመምታት አስቦ ቦታ ሲያጣ ለበረከት ግዛው አቀብሎት በረከት ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ የሚጠቀስ የጎል ዕድል ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ በ54ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው የመጀመርያ ጎል ብርቱካናማዎቹ አስቆጥረዋል። ከቀኝ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሐመድ የመታውን ግብ ጠባቂው ፋሲል ኳሱን ለመቆጣጠር ዘሎ የተፋውን አስራት ቱንጆ አግኝቶ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ተመጣጣኝ የሆነ የማጥቃት ምልልሶች በሁለቱም በኩል ቢያስመለክቱንም በአንፃራዊነት ዐፄዎቹ ተቀይሮ በገባው ኬዛ እና ጌታነህ ከበደ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ብዙም ፍሬያማ መሆን አልቻሉም። በዚህ ሂደት 75ኛው ደቂቃ ማርቲን ኪዛ ያሻገረለትን ጌታነህ ከበደ ኳሷን ተቆጣጥሮ ወደ ጎል የመታውን አህመድ ረሺድ ኳሷን በእጁ ነክቶ አቅጣጫዋን አስቶታል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄ ካቀረቡበት እንቅስቃሴ ውጭ የጠሩ ሙከራዎችን ለማድረግ በእጅጉኑ ተቸግረው ታይተዋል።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ፋሲሎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው የሚወጡበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ሲፍጨረጨሩ ቢታይም የድሬዳዋን የመከላከል አጥር አልፈው መረቡን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በድሬዳዋ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።