በመጀመሪያው አጋማሽ 5 ጎል ባስመለከተን ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች መቐለ 70 እንደርታን 4-1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባህር ዳር ከተማን ከ መቐለ 70 እንደርታ ያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ነበር። ባህር ዳር ከተማዎች ባለፈው ሳምንት በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ ማግስት ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ሲሆን በተመሳሳይ መቐለ 70 እንደርታዎች ባለፈው ሳምንት ሀድያ ሆሳዕና ላይ ያሳኩትን ድል ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ከጅማሮው አንስቶ የግብ ናዳዎችን ያስመለከተን ጨዋታ ነበር። ከሽንፈት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ባህር ዳር ከተማዎች በጨዋታ እና በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ በመውሰድ ሙሉ ጨዋታን በሚባል መልኩ መቆጣጠር ችለዋል። ጥሩ ጨዋታን ሲያስመለክቱን የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች ገና በጊዜ በ4ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ግባቸውን አሃዱ ብለው ጀምረዋል። ፍፁም ፍትሕአለው በጥሩ እይታ ያቀበለውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ከግብ ጠባቂው በመገናኘት የሞከረው ኳስ ቢመለስበትም ድጋሚ የተመለሰውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የጣና ሞገዶችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ብዙም ሳይቆይ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ መቐለዎች ለማጥቃት የወሰዱትን ኳስ ባህር ዳሮች በማስጣል በመልሶ ማጥቃት ያገኘኙትን ኳስ ፍፁም ዓለሙ የሜዳው የመሃል ክፍል ላይ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ወንድወሰን በለጠ ከግብጠባቂው ጋር ፊትለፊት ተገናኝቶ ግብ የሚያስቆጥርበት ዕድል ቢኖረውም ግን ከእሱ ይልቅ ምቹ ሁኔታ ላይ ላለው አቤል ማሙሽ በመስጠት አቤል ባስቆጠረው ግብ መሪነታቸውን በሁለት ጎል ልዩነት ማድረግ ችለዋል።
በመልሶ ማጥቃት ምህረት አልባ የሆኑት ባህርዳር ከተማዎች በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ሶስተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ እና ፍፁም ዓለሙ በአንድ ሁለት ቅበብል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ፍፁም ዓለሙ ያቀበለውን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ጥሩ በሚባል አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ወደ ለራሱ ሁለተኛ ለክለቡ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥሯል።
የግብ ድብደባቸውን ማድረግ ያላቆሙት ባህርዳር ከተማዎች 37ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ያደረገው ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሳ ከመቐለ ተከላካዮች ጋር በመታገል ያቀበለውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ ያገኘው አቤል ማሙሽ ሁለተኛ ግቡን በማስቆጠር መሪነቱን ወደ አራት ጎል ልዩነት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ከዚህ ሁሉ የግብ ዕዳ በኋላ ራሳቸውን አረጋግተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ የሞከሩት መቐለዎች ከብሩክ ሙሉጌታ ያለቀለት የግብ ሙከራ በኋላ 42ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥው ውጪ ንኮዋ ሐፕሞ አክርሮ የመታውን እና ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ የመለሰውን እና መቆጣጠር የከበደውን ኳስ አሸናፊ ሐፍቱ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ያለግብ ከመውጣት ታድጓል። የመጀመሪያው አጋማሽም በባህርዳሮች 4-1 መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች ራሳቸውን አሻሻለው መቅረብ የቻሉ ሲሆን በተደጋጋሚ በቁጥር በመብዛት የባህርዳሮችን የግብ ክልል መጎብኘት ችለዋል ሆኖም ግን ያስቆጠርነው ግብ ይበቃናል በማለት መከላከሉ ላይ ምርጫቸው በማድረግ የሚጫወቱትን የባህርዳር ተከላካዮች ማለፍ እና ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በአጋማሹ ምንም አይነት ግብ ሳያስመለክቱን ጨዋታዎ በጣና ሞገዶች 4-1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።