የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ መቻልን የገጠመው ሲዳማ ቡና በመለያ ምት 7ለ6 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።
ቀን 9:30 ሲል በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የጀመረው ተጠባቂው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በኳስ ቁጥጥር ብልጫ እየተፈራረቁ የወሰዱ ቢሆንም የግብ ማግባት ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ ለተመልካች አስመልክተዋል። ጥንቃቄ በተሞላ መንገድ በቀጠለው በመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታው እስከ 15 ደቂቃ እስኪዘልቅ ድረስ በፈጣን ሽግግር ቡድኖቹ ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል መድረሳቸውን ቢቀጥሉም ይሄ ነው ተብሎ የሚገለፅ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ይቅሩ እንጂ መቻሎች ከባድ ሙከራ በ15ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል፤ ዳዊት ማሞ እና በረከት ደስታ ባደረጉት ቅብብል ዳዊት ማሞ ወደ ሳጥን አሻምቶ አቤል ነጋሽ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ ቢመታም የሲዳማ ቡና ተከላካዮች እንዴትም ተረባርበው አግደውበታል።
ሲዳማ ቡናማዎችም ቶሎ ቶሎ ወደ ሳጥን እየደረሱ ነገር ግን ወደ ግብ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ተስነኗቸው ጨዋታው የአጋማሹ አካፋይ ላይ ሲደርስ ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አከታትለው አድርገዋል፤ በ22ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰና ብርሀኑ በቀለ ባደረጉት ቅብብል መስፍን ታፈሰ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የመታት ኳስ ለጥቂት ከግቡ ቋሚ ብረት ርቃ ያለፈችበት ፤ እንዲሁም በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሬድዋን ናስር ሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ የመታት ኳስ ተጫራርፋ ሳሙኤል ሳሊሶ ጋር ደርሳ ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቀላሉ የተቆጣጠረበት አጋጣሚ ሲዳማ ቡናዎቹን መሪ ለማድረግ የቀረበ አደገኛ ሙከራ ነበር።
አጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ማግባት ፍላጎታቸው አጠናክረው ቀጥለው በመልሶ ማጥቃት ወደፊት በመድረስ ረገድ እንዲሁም የተሳካ ቅብብል በማድረግ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም እንቅስቃሴዎሳቹ ወደ ግብነት ለመቀየር ሲቸገሩ አስተውለናል። መቻሎች በአንፃራዊነት ከሜዳው ወረድ ብለው ኳስ ከግብ ጠባቂያቸው ጀምረው መስርተው ሲጫወቱ አስተውለናል። እንዲሁም በቁጥር በርከት ያሉ የቆሙ ኳሶችን ማግኘት ችለዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ኮሊን ኮፊ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው አደገኛው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። አጋማሹም ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከመልበሻ ክፍል መልስ መቻሎች ጠንከር ብለው ገብተው የኳስ ቅብብል ብልጫ የወሰዱበትን የሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ አምስት ደቂቃዎችን አሳልፈዋል፤ በተለየም በ50ኛው ደቂቃ ላይ ኮሊን ኮፊ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ የሲዳማ ቡናው የግብ ዘብ መስፍን ሙዜ በግሩም ሁኔታ ወደ ውጪ ያወጣባቸው ሙከራ ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያው ከባዱ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል። ሲዳማ ቡናዎች በአንፃራዊነት በፈጣን ሽግግር ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ ያስተዋልን ቢሆንም ጠንካራ ሆኖ የዋለውን የመቻልን የኋላ ደጀን አልፎ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ አስተውለናል።
የግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው የቀጠሉት መቻሎች በ55ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ በበረከት ደስታ አማካኝነት አድርገዋል፤ በተጠቀሰው ደቂቃ ዳዊት ማሞ በግራ መስመር በኩል ለነበረው በረከት ደስት ኳስ አቃብሎት በረከት ደስታ በግሩም ሁኔታ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ ሲመታ በንቃት ሲጠባብቅ የነበረው የግቡ ዘብ እንዴትም አግዶበታል። እራሱን ኳስ መቻሎች ድጋሚ አግኝተው በረከት ደስታ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ሽመልስ በቀለ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ ርቆ አልፎባቸዋል። ሲዳማ ቡና ቡናዎችም በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ59ኛው ደቂቃ ላይ ሬድዋን ናስር እና ማይክል ኪፕሩቪ ባደረጉት ቅብብል ማይክል መሬት ለመሬት መትቶ ያደረገው ሙከራ ሌላኛው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
ከእንቅስቃሴ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እየተንቀሳቀሱ የቀጠሉ ቢሆንም ወደ ፊት ሄደው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸው ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አቅኝቷል። ግብ የሚያስተናግድ እየመሰለ በቀጠለው በጨዋታው መቻሎች በቆሙ ኳሶች ሙከራዎችን ለማድረግ በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉ ቢሆንም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው መለያ ምት ቡና 7ለ6 በሆነ ውጤት አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።