ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በነበረው ጨዋታ በዕለቱ ዳኛ የቀይ ካርድ ተመልክተው የነበሩት የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ ከባድ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
በሀያ አምስተኛ ሳምንት መደረግ የነበረበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በዝናብ እና መብራት የተነሳ ሦስት ቀናቶች ከፈጀ በኋላ በትላንትናው ዕለት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከትላንት በስቲያ ዕለተ ዕሁድ ጨዋታው እየተደረገ በመጀመሪያው አጋማሽ የጭማሪ ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ከዕለቱ ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት በተከታታይ ከተመለከቱት ቢጫ በኋላ በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዳቸው የሚታወስ ሲሆን ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሲያመራም ሌሎች ንትርኮች እንደነበሩ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በተስተካካዩ ጨዋታ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ይታገሱ እንዳለ ቡድናቸው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በነበረው የ25ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ የዕለቱን ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው በዳኞች የመልበሻ ክፍል አካባቢ ተመሳሳይ ድርጊትን የፈፀሙ በመሆኑ ዋና አሰልጣኙ ቀይ ካርድ ለተመለከቱበት ሦስት ጨዋታ እንዲታገዱ እና አስር ሺህ ብር እንዲከፍሉ እንዲሁም አፀያፊ ስድብ ለተሳደቡበት ጥፋት ደግሞ ስድስት ጨዋታ እንዲታገዱ እና አምስት ሺህ ብር እንዲከፍሉ በድምሩ ዘጠኝ ጨዋታ እንዲታገዱና አስራ አምስት ሺህ ብር እንዲክፍሉ ተወስኗል።
በተያያዘ መረጃ ቢጫ ካርድ በተመለከቱ አሰልጣኞችም ላይ ተጨማሪ ቅጣቶች ሲተላለፉ የአርባምንጩ አሰልጣኝ በረከት ደሙ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ ረዳት አሰልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ አንድ አንድ ጨዋታ ታግደዋል።